الوصف
رسالةٌ مختصرةٌ مترجمة للغة الأمهرية بيَّن فيها المُؤلِّف - أثابه الله - ما يأمرنا به الإسلام وأعظمها أركانَ الإيمان الستة وبعض العبادات والمعاملات التي يجب أن تتوفر في كل مسلم، وكل هذا بأسلوبٍ سهل، دقيق العبارة، مُبتعدًا عن التطويل والتفريع، وهو مفيد للناشئة والشباب ومن ليس عنده وقت للتوسُّع في كتب العقيدة والآداب الإسلامية.
ترجمات أخرى 51
المحاور
እኔ ሙስሊም ነኝ
ፀሐፊ ዶ/ር ሙሐመድ ቢን ኢብራሂም አልሐመድ
ሙስሊም ነኝ፤ ማለትም ሃይማኖቴ እስልምና ነው።እስልምና ነብያቶች ከመጀመሪያቸው እስከ መጨረሻቸው ሲቀባበሉት የመጣ ፍፁም (ሃይማኖትን የሚገልፅ) ታላቅ ቃል ነው።ይህ ቃል ምጡቅ መልዕክቶችንና ታላላቅ ሀሳቦችን ያካተተ ቃል ነው።ቃሉ ሁሉንም ለፈጠረው አምላክ መማረክን፣ ለትዕዛዛቱ መጎተትንና ታዛዥ መሆንን የሚገልጽ ነው።ከማህበረሰብም ከግለሰብም አኳያ ሰላም፣ መረጋጋትንና ስኬታማነትን እንዲሁም ደህንነትንና እርካታን የሚገልፅ ነው።
በመሆኑም ነው በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ተደጋጋሚ ከሆኑ ቃላቶች መካከል "ሰላም" እና "እስልምና" የሚሉት ቃላት የሆነው።"አስ-ሰላሙ" የሚለውም ከአላህ ስሞች መካከል አንዱ ነው።ሙስሊሞች በመካከላቸው የሚለዋወጡት ሰላምታም "ሰላምን" ነው።የጀነት ሰዎችም የሚለዋወጡት ሰላምታ (ሰላምን) ነው።ትክክለኛ ሙስሊም የሚባለውም፥ ሙስሊሞች ከእጁም ሆነ ከምላሱ ሰላም ያገኙበት ሰው ነው።እስልምና ለመላው ለሰው ልጅ መልካም የሆነ ሃይማኖት ነው። በቂያቸውም ነው። በዱኒያም በአኺራም የስኬታቸው መንገድም ነው።ስለዚህም ነው የትኛውንም ዘር ከሌላኛው ዘር፤ አንዱን የቆዳ ቀለም ከሌላኛው የቆዳ ቀለም ሳይለይ ሁሉንም በአንድ ዓይን የሚያይ አካታች፣ ሰፊና ግልፅ እንዲሁም ለሁሉም ክፍት ሆኖ የመጣው።ማንም ቢሆን ከእስልምና አስተምህሮ በያዘው ልክ ካልሆነ በቀር አይለያይም።
ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ በመሆኑም የተስተካከለ አመለካከት ያለው ሁሉ ይቀበለዋል።የሰው ልጅ ሁሉ በመልካምነት፣ በፍትህ፣ በነፃነት፣ ጌታውን የሚወድና የፈጠረው አምላክ አምልኮ እንደሚገባውና ከእርሱም ውጭ ሊመለክ የሚገባው የሌለ መሆኑን የሚያምንበት ሆኖ ነው የሚፈጠረው።ይህንንም ተፈጥሮውን የሚቀይር አንዳች ጋሬጣ ካልገጠመው በቀር ከዚህ ተፈጥሮው አይወጣም።ይህንኑ ሃይማኖት መርጦ የወደደላቸውም የሰው ልጆች ፈጣሪ፣ ጌታና አምላካቸው ነው።
በዚች ዓለም ለተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ከሞት በኋላ ወደ ሌላ ሀገር እንደምዘዋወር እና በዛች ሀገርም የሰዎች መመለሻቸው ወይ ወደ ጀነት ወይ ወደ ጀሀነም እንደሆነ እስልምና ሀይማኖቴ ያስተምረኛል።
በሚያዘኝ ጉዳዮች እያዘዘ እርም ከሆኑ ጉዳዮችም የሚከለክለኝ እስልምናዬ ነው።በሚያዘኝ ጉዳዮች ታዝዤ ከሚከለክለኝ ጉዳዮችም ከተከለከልኩኝ በዱኒያም በአኺራም ህይወቴ ደስተኛ እሆናለሁ።ከተሰጠኝ መመርያ ካፈገፈግኩኝም በዱኒያዬም በአኺራዬም ባፈገፈግኩበት ልክ እድለቢስ እሆናለሁ።
እስልምና ያዘዘኝ ትልቁ ጉዳይ አላህን በብቸኝነት እንድገዛው ነው።እኔም ፈጣሪዬም አምላኬም አላህ መሆኑን ቁርጥ ባለ መልኩ እመሰክራልሁ።እርሱኑ ወድጄ፤ ቅጣቱንም ፈርቼ፤ ምንዳውንም ከጅዬ፤ በርሱም ላይ ተመክቼ የማመልከው አላህን ብቻ ነው።ይኸው ተውሒድ፥ አላህን በብቸኝነቱ ነቢዩ ሙሐመድን ደግሞ መልዕክተኛው መሆናቸውን በመመስከር ላይ የተመሰረተ ነው።ነቢዩ ሙሐመድ፥ አላህ ለዓለማት እዝነት አድርጎ የላካቸው፤ ነቢይነትንም መልዕክተኝነትንም በእርሳቸው የደመደመባቸው፤ ከእርሳቸውም በኋላ ሌላ ነቢይ የሌለ የአላህ መልዕክተኛ ናቸው።ለየትኛውም ዘመን፣ ቦታም ይሁን ማህበረሰብ የሚሆን አካታች የሆነ ሀይማኖትን ነው ይዘው የመጡት።
ሃይማኖቴ፥ በመላእክቶችና በመላው መልዕክተኞች ከእነርሱ መካከልም በነቢዩ ኑሕ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ዒሳና ሙሐመድ በሁሉም እንዳምን በቆራጥ መመርያ አዞኛል።
በመልዕክተኞች በወረዱት ሰማያዊ ኪታቦች እንዳምንና የመጨረሻቸውና መደምደሚያቸው የሆነውን ቁርኣንንም እንድከተለው ያዘኛል። ከመጽሐፍቱ መካከል ታላቁ (የተከበረው ቁርኣን) ነው።
ሰዎች እንደየስራቸው የሚመነዱበት በሆነው የመጨረሻው ቀንም እንዳምን ያዘኛል።በቀደርም (በአላህ ውሳኔ) እንዳምንና በዚህችው ዓለም በሚሆነው በጎም ሆነ ክፉም ነገር ወድጄ ተቀብዬ ለመዳን የሚያስችለኝን ሰበብም እንዳደርስ ያዘኛል።
በቀደር ማመኔ እርካታን፣ እርጋታንና ትዕግስትን አላብሶ ባለፈ ነገር እንዳልቆጭ ያደርገኛል።ምክንያቱም ያጋጠመኝ ሊስተኝ እንዳልነበር፤ ያመለጠኝ ደግሞ ሊያጋጥመኝ እንዳልነበር አስረግጬ አውቃለሁና።ሁሉም ነገር በአላህ የተወሰነና የተፃፈ እንደመሆኑ መጠን እኔ የሚጠበቅብኝ ሰበቡን አድርሼ ከዛ በኋላ የሚሆነውን ወድጄ መቀበል ነው።
እስልምና መንፈሴን በሚያጠራ መልካም ስራና ጌታዬንም በሚያስደስት፣ ነፍሴንም በሚያጠራ፣ ቀልቤንም በሚያስደስት፣ ልቦናዬንም በሚከፍት፣ ጎዳናዬን በሚያበራልኝ፣ በማህበረሰቡ መካከልም ጠቃሚ በሚያደርገኝ መልካም ስነ ምግባር ሁሉ የሚያዘኝ ነው።
ከእነዚህ መልካም ስራዎች ሁሉ የላቁት፥ አላህን በብቸኝነት ማምለክ፣ በቀንና በሌሊት የሚሰገዱትን አምስት ሰላቶችን አሟልቶ መስገድ፣ የገንዘብ ዘካን መስጠት፣ በየአመቱ አንድ ወር ይኸውም የረመዷንን ወር መፆም፣ ሐጅ ማድረግ ለቻለ ሰው በመካ የሚገኘውን የአላህን ቤት መጎብኘት ነው።
ልቦናዬን ክፍት ከሚያደርጉልኝ ሃይማኖቴ ከጠቆመኝ ታላላቅ ጉዳዮች መካከል፥ የአላህ ቃል፣ ከንግግሮች ሁሉ እውነተኛ፣ እጅግ ያማረና ምጡቅ፣ የቀደምቶቹንም የኋለኞቹንም እውቀት አጠቃሎ የያዘ የሆነውን ቁርኣንን መቅራት ማብዛት ይገኝበታል።ቁርኣንን ማንበብ እና ማዳመጡ የሚያነብው ወይም የሚያደምጠው ዓረብኛን አሳምሮ የማይችል ወይም ጭራሽ ሙስሊም ባይሆን ራሱ በልብ ውስጥ እርጋታን፣ እርካታንና ደስተኝነትን ይፈጥርለታል።
ዱዓእ እና ወደ አላህ መዋደቅን ማብዛት እንዲሁም ለትልቁም ለትንሹም ጉዳይ እርሱን መጠየቅ ልቦናን ክፍት ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል የሚጠቀስ ጉዳይ ነው።አላህ ዒባዳን ለርሱ ብቻ ጥርት አድርጎ ለተማፀነው ሰው ሁሉ ምላሽ ይሰጣል።
ልቦናን ክፍት ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ልዕለ ኃያሉ አላህን አብዝቶ ማውሳት ይገኝበታል።
የኔ ነብይ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን አላህን እንዴት ማውሳት እንደምችልና ይበልጥ የማወድስበትን አኳኋን በሚገባ አስተምረውኛል።ከእነዚህም መካከል ከቁርኣን ቀጥሎ በላጭ የሚባሉት አራቱን ቃላት መጥቀስ ይቻላል። እነርሱም: ("ሱብሓነላህ" [ለአላህ ጥራት ይገባው]፣ "አልሐምዱ ሊላህ" [ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው]፣ "ላ ኢላሃ ኢለሏህ" [ከአላህ በስተቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም]፣ "አላሁ አክበር" [አላህ ታላቅ ነው።]) ናቸው።
እንዲሁም ("አስተግፊሩላህ" [አላህ ሆይ! ምህረትህን እማፀንሀለሁ] እና "ላ ሐውላ ወላ ቁወተ ኢላ ቢላህ" [በአላህ ካልሆነ በቀር ብልሀትም ይሁን ሀይል የለም።])
እነዚህ ቃላት ልቦናን በመክፈትና ቀልብ ውስጥ እርካታ እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው።
እስልምና ደረጃዬን ከፍ እንዳደርግና ስብእናዬንም ይሁን ክብሬን ከሚያወርድ ነገርም እንድርቅ ያዘኛል።አዕምሮዬንም ይሁን አካላቴንም ለተፈጠርኩለት በዱኒያም በአኺራም ለሚበጅ በጎ ስራ እንዳውለው ያዘኛል።
እስልምና ከፍጡራን ጋር ባለኝ መስተጋብር በቻልኩት ልክ በቃልም ይሁን በተግባር እዝነት፣ መልካም ስነምግባር እና በጎ መኗኗርን እንድላበስ ያዘኛል።
ከታዘዝኩባቸው የፍጡራን መብቶች መካከል ትልቁ የወላጆች መብት ነው። ለእነርሱ መልካም እንድሆን፣ መልካሙንም እንድወድላቸው፣ ለደስታቸው እንድተጋ እና የሚጠቅማቸውን ሁሉ እንዳቀርብላቸው ሃይማኖቴ አዞኛል። በተለይም በሚያረጁበት ጊዜ።እናት እና አባት ልጆቻቸው ዘንድ ከፍተኛ የምስጋና፣ የአክብሮት እና የአገልግሎት ደረጃ አግኝተው የምታገኛቸው በኢስላማዊ ማህበረሰብ ዘንድ የሆነበት ምክንያት ይሀው ነው።ወላጆች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ወይም ሲታመሙ ወይም አቅም እየተሳናቸው በሄዱ ቁጥር ልጆችም እነርሱን በተመለከተ ያላቸው ኅላፊነትም እየጨመረ ይሄዳል።
ሴቶች ትልቅ ክብር እና ትልቅ መብት እንዳላቸውም ሃይማኖቴ አስተምሮኛል።በእስልምና ሴቶች የወንዶች ክፋይ ናቸው፤ ከሰዎችም በላጩ ለቤተሰቦቹ መልካም የሆነው ነው።ሙስሊም ሴት በልጅነቷ የእናቷን ጡት መጥባት፣ እንክብካቤና ጥሩ አስተዳደግ የማግኘት መብት አላት። በዚያን ጊዜ እርሷ ለወላጆቿም ይሁን ለወንድሞቿ የዓይን ማረፊያና የልባቸው ዋና ነች።
ባደገች ጊዜም አሳዳጊዋ በስስት ዓይን የሚከታተላት በእንክብካቤውም የከበባት የተከበረች እና የተወደደች ናት።በመሆኑም ክፉ እጆች ወደ እርሷ እንዲዘረጉ፣ አስቸጋሪ ምላስም እንዲለክፋት፣ አታላይ ዓይንም እንዲሸውዳት አይፈልግም።
ብታገባም ይህ የሚሆነው በአላህ ቃል መሰረትና በታላቅ ቃል ኪዳን ነው።በመሆኑም በለቤቷ ቤት በታላቅ መጎዳኘት ውስጥ ትኖራለች።ባለቤቷም ሊያከብራት፣ በበጎ ሊኗኗራትና እርሷን ከማስቸገር ሊቆጠብ ግዴታው ነው።
እናት በሆነች ጊዜ ደግሞ ለርሷ በጎ መዋል ከላቀው አላህ መብት ጋር የተጣመረ መብቷን መፈፀም ሲሆን እርሷን አለመታዘዝና ማጎሳቆልም በምድር ላይ ብክለትን ከማንሰራፋትና ሽርክ ጋር የተቆረኘ በደል መፈፀም ነው።
እህት በሆነችም ጊዜ፥ ሙስሊሙ እንዲደግፋት፣ እንዲያከብራት እና ክፋት እንዳያጋጥማት እንዲንከባከባት የታዘዘችበት ናት።አክስት ስትሆንም በፅድቅና መልካም በመሆን ረገድ ከእናት ጋር እኩል ትሆናለች።
ሴት አያት ወይም አዛውንት ሴት ስትሆን ደግሞ በልጆቿ፣ በልጅ ልጆቿ እንዲሁም በዘመዶቿ ሁሉ ያላት ደረጃ ከፍ ያለ ይሆናል። ፍላጎቷ ችላ የሚባል አስተያየቷም ቀለል የሚደረግ አትሆንም።
ዝምድናዋ ወይም ጉርብትናዋ ራሱ ራቅ ያለም ቢሆን በጥቅሉ እንደ ሙስሊምነቷ እርሷን ከማስቸገር ሊቆጠቡና ዓይንን ዝቅ ሊያደርጉላት የመሳሰሉት መብቶች አላት።
ሙስሊሞች እነዚህን ሙስሊም ባልሆኑ ማህበረሰቦች ዘንድ የማይገኙ እሴቶችን በሚገባ እየተወጡ ሴት ልጅ የተሰጣትን ሐቅ በሚገባ ጠብቀው ይዘዋል።
በተጨማሪም ሴቶች በእስልምና ከሃይማኖታቸው ጋር እስካልተቃረነ ድረስ ንብረት የማፍራት፣ የመከራየት፣ የመሸጥ፣ የመግዛት እና ሌሎች ውሎችንም የመዋዋል እንዲሁም የመማር፣ የማስተማርና የመስራት መብቷ የተጠበቀ ነው።አረ እንደውም በግለሰብ ደረጃ ሊያውቁትና ወንድም ሆነ ሴት ቢተውት ኃጢኣተኛ የሚሆኑበት የእውቀት ዓይነትም አለ።
ይልቁንም ሁሉንም አፈጣጠራቸውን በሚመጥን መልኩ ወንዶችን ብቻ ለይቶ በመጣ ወይም ሴቶችን ብቻ ለይቶ በመጣ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለወንዱ ያለው መብት ሁሉ ለእርሷም አላት።
ሃይማኖቴ ወንድሞቼን፣ እህቶቼን፣ የአባቴን ወንድምና እህቶች፣ የእናቴን ወንድምና እህቶች እና ዘመዶቼን ሁሉ እንድወድ አዝዞኛል። የሚስቴን፣ የልጆቼን እና የጎረቤቶቼንም መብት በሚገባ እንድጠብቅ ያዘኛል።
ሃይማኖቴን እንድማር ያዘኛል። አእምሮዬ፣ ስነምግባሬንና አመለካከቴንም በሚያበለፅግ ነገር እንድገኝም ያዘኛል።
ዓይነ አፋርነት፣ የዋህነት፣ ለጋስነት፣ ጀግንነት፣ ጥበበኛነት፣ ጨዋነት፣ ትዕግስት፣ ታማኝነት፣ ትህትና፣ ጥብቅነት፣ ንፁህነት፣ ቃል ጠባቂነትን እንድላበስ ያዘኛል። ለሰውም በጎ እንድመኝ፣ ኑሮን ለማሸነፍ እንድጣጣር፣ ለተቸገሩ ቸር እንድሆን፣ ህመምተኛንም እንድጠይቅ፣ ቃሌን እንድሞላ፣ መልካም ተናጋሪም እንድሆን፣ በፈገግታ የተሞላ ፊትም እንዲኖረኝ እና የምችለውን ያህል እያደረግኩኝም ሰዎችን ላስደስት ታዝዣለሁ።
በአንጻሩ ደግሞ ከድንቁርና ያስጠነቅቀኛል፣ ከክህደት፣ ከአፈንጋጭነት፣ ከማመፅ፣ ከብልግና፣ ከዝሙት፣ ከጠማማነት፣ ከትዕቢት፣ ከምቀኝነት፣ ሰዎችን ከመጥላት፣ ሰዎችን በክፉ ከመጠርጠር፣ ከክፉ አሳቢነት፣ ከሀዘን፣ ከቅጥፈት፣ ተስፋ ከመቁረጥ፣ ከስስታምነት፣ ከስንፍና፣ ከፈሪነት፣ ከአውደልዳይነት፣ ቁጡ ከመሆን፣ ከመጃጃልና ሞኛሞኝ ከመሆን፣ ሰውን ከማስከፋት፣ እርባና ቢስ ወሬ ከማብዛት፣ ምስጢር ከማባከን፣ ከውለታቢስነት፣ ቃል ኪዳንን ከማፍረስ፣ ወላጆችን ከማመፅ፣ ዝምድና ከመቁረጥ፣ ልጆችን ከማጉላላት ጎረቤትን ከማስቸገር እና አጠቃላይ ፍጡራንን ከማስቸገር ከልክሎኛል።
በተጨማሪም እስልምና አስካሪ መጠጦችን ከመጠጣት፣ እፅ ከመጠቀም፣ በገንዘብ ቁማር ከመጫወት፣ ከስርቆት፣ ከማጭበርበር፣ ከማታለል፣ (በቀልድ ስም) ሰዎችን ከማስደንገጥ፣ ሰዎችንም ከመሰለል እና ነውራቸውን ከመከታተልም ከልክሎኛል።
ሃይማኖቴ እስልምና ለገንዘብም ጥበቃ ያደርጋል፤ በዚህም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ይረዳል፤ ለዛም ነው አደራ ጠባቂነትን እያበረታታ አደራ ጠባቂዎችንም የሚያወድሰው፤ በዱኒያ መልካም ሕይወትን እንደሚኖሩና በአኺራም ጀነት እንደሚገቡ ቃል የሚገባላቸው። ስርቆትንም ይከለክላል፤ ስርቆት ላይ ለተሰማራም በዱንያም በአኺራም ቅጣት እንዳለበት ይዝታል።
ሃይማኖቴ ህይወትንም ይታደጋል። ስለዚህም ነው ያለአግባብ ነፍስን ማጥፋት፤ በሌሎች ላይም በየትኛውም መልኩ በቃልም ቢሆን ድንበር ማለፍን የሚከለክለው።
ከዛም አልፎ የሰው ልጅ በራሱ ላይም ቢሆን ድንበር ማለፉን ይከለክላል። በመሆኑም የሰው ልጅ አእምሮውን የሚበክል፣ ወይም ጤናውን የሚያውክ ነገር ሊያደርግ አልያም ራሱን ማጥፋት አይፈቀድለትም።
እስልምና ሃይማኖቴ፥ የነፃነት ዋስትና ያረጋግጣል፤ ስርዓትም ያስይዘዋል።የትኛውም ሰው በእስልምና የተከለከለን ነገር እስካልሆነ ድረስ የማሰብ፣ የመሸጥ፣ የመግዛት፣ የመገበያየት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነቱ የተረጋገጠ ነው። ራሱንም ይሁን ሌሎችን የሚጎዳ ሐራም ነገር እስካልሆነ ድረስ በመብላት፣ በመጠጣት፣ በመልበስ እና በማዳመጥ ህይወቱን ዘና የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ይችላል።
ሃይማኖቴ የነፃነት መስመርን ያስተካክላል። ማንም ሰው ሌላውን እንዲበድል አይፈቅድም፤ ወይም አንድ ሰው ገንዘቡን፣ ደስታውን ወይም ሰብአዊነቱን የሚያደፈርሱ ሐራም መዝናኛዎችን ማድረግን አይፈቅድም።
ሃይማኖትም ይሁን ህሊና ሳይገድባቸው ራሳቸውን በሁሉም ነገር ልቅ ያደረጉ ሰዎችን ያሉበትን ሁኔታ ከተመለከትካቸው በዘቀጠ የመከራና የጭንቀት ደረጃ ውስጥ እየኖሩ ነው የምታገኛቸው። አንዳንዶቹንማ ካሉበት ጭንቀት ለመገላገል ሲሉ ራሳቸውን ማጥፋት የሚፈልጉ ሆነው ታገኛቸዋለህ።
ሃይማኖቴ የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመተኛት እና ከሰዎች ጋር የመነጋገርን ከሁሉም የላቀ የሆነውን ስርዓት ያስተምረኛል።
ሃይማኖቴ በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም መብትን በመጠየቅም በኩል ገራገርነትን ያስተምረኛል።ሃይማኖቴን ካልተቀበሉ ሰዎች ጋርም ገራገርነትን እንድላበስ ያስተምረኛል። እነርሱን እንዳልበድላቸውና እንዳላስቀይማቸው፤ ይልቁንም መልካምን እንዳደርግላቸው፤ መልካምም እንዲገጥቸው እንድመኝ ያስተምረኛል።
ከእነርሱ በፊት የትኛውም ህዝብ አድርጎት የማያውቅን ገራገርነት ሙስሊሞች ለሚቃረናቸውም ቢሆን እንዳላቸው ታሪክ ይመሰክራል።ሙስሊሞች ከእነርሱ የተለየ እምነት ካላቸው ህዝቦች ጋርም አብረው ኖረዋል። ሌሎችንም በሙስሊሞች ቁጥጥር ስር አድርገው ኖረዋል። ሙስሊሞቹ ታዲያ - ከሁሉም ጋር - በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ያማረ አኗኗር ሲኖሩ ነው የነበሩት።
ባጭሩ እስልምና ህይወቴን ፍፁም የማደርግበትን እና ተድላዬን የሚያሟላ ምጡቅ ስነ-ምግባርን፣ ቀና አስተሳሰብን እና የላቀ ስነስርዓትን እንድላበስ አስተምሮኛል።ህይወቴን ከሚያውኩ እና ማህበራዊ ኑሮን ከሚያቃውስ አካልን፣ ነፍስን፣ አእምሮን፣ ገንዘብን፣ ክብርን እና መኗኗርን ከሚጎዳ ነገር ሁሉ ከልክሎኛል።
እኔም እነዚህን አስተምህሮ ተግባራዊ ባደረግኩት ልክ ደስተኝነትን እጎናፀፋለሁ።ከአስተምህሮቱ በየትኛውም በኩል ባለኝ ቸልተኝነት እና ስልቹነት ልክ የራቅኩትን ያህል ደስታዬም ይቀንሳል።
ባሳለፍኩት የህይወት መስመር እኔ ስህተት ላይ ያልወደቅኩ ጥብቅ ነኝ ማለት አይደለም። ሃይማኖቴም ቢሆን ሰው እንደመሆኔ መጠን በደካማነቴ አንዳንድ ጊዜ ስህተት ላይ እንደምወድቅና ጉድለቶችም እንዳሉብኝ ግምት ውስጥ ያስገባል። በመሆኑም የተውባ (ንስሐ)፣ የመሀርታ መጠየቂያና ወደ አላህ የመመለሻ በር ከፍቶልኛል። ተውባ ማድረግ (ንስሀ መግባት) የጉድለቴን ፋና ይሰርዛል፤ ጌታዬ ዘንድ ያለኝን ደረጃም ከፍ ያደርጋል።
ሁሉም የእስልምና ሃይማኖት የእምነት፣ የምግባር፣ የስነምግባር እና የግብይት አስተምህሮዎች ሁሉ ከተከበረው ቁርኣን እና ከተጣራ ሱና የመነጩ ናቸው።
በመጨረሻም እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ጉዳይ ቢኖር፡- ማንም ሰው በየትኛውም አለም ላይም ቢሆን የእስልምናን ሃይማኖት ለእውነት በፍትህ እና በገለልተኝነት አይን ቢያየው ኖሮ ከመቀበል በቀር ምንም አማራጭ የማያገኝለት ሃይማኖት እንደሆነ ነው። ችግሩ ግን የእስልምና ሃይማኖት በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ወይም በአንዳንዶቹ የምርተከታዩ ባልሆኑ አካላት ድርጊት የሚጠለሽ መሆኑ ነው።
እንጂ ማንም ቢሆን የእስልምናን እውነታ በትክክል ቢያየው ወይም እስልምናን በትክክል የሚተገብሩትን የሃይማኖቱን ሰዎች ሁኔታ ከተመለከተ እስልምናን ለመቀበል እና ወደ እስልምና ለመግባት አያቅማማም ነበር።እስልምና ለሰው ልጅ ደስታ፣ ሰላምና ደህንነት፣ ፍትህ እና በጎነትን ለማስፈን የመጣ ሃይማኖት እንደሆነም ግልፅ ይሆንለት ነበር።
ከእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ጥቂቶችም ይሁኑ ብዙዎች የሚያጠፉትን ጥፋት በምንም አይነት ሁኔታ ለሃይማኖቱ መወቀሻ ወይም መተቻ አይሆንም። ይልቁንም ሃይማኖቱ ከእነርሱ የፀዳ ነው።የማፈንገጣቸው መዘዙ ወደ ራሳቸው ጥመት የሚመለስ ነው። ምክንያቱም እስልምና እንዲህ እንዲያደርጉ አላዘዛቸውምና፤ ይልቁንም ሃይማኖቱ ካመጣው መመርያ ማፈንገጥን ከልክሏቸዋል።
ከዛም ባሻገር ስለ ሃይማኖቱ ለማወቅ ፍትሃዊነት የሚመራው ሃይማኖቱን በትክክል የተገበሩ ሰዎችን፣ እነርሱንም ይሁን ሌላውን በተመለከተ ለትእዛዛቱ ያደሩ ሰዎችን እንዲመለከቱ ነው። ምክንያቱም ይህን ማድረጋቸው ለሃይማኖቱ ክብርና ሞገስን እንዲሰጡ ይረዳቸዋልና።እስልምና ትንሹንም ትልቁንም መመሪያና ስርዓት ሳያዝበት፤ የትኛውንም ብልግናና ብክለትንም ሳያስጠነቅቅበትና ከመዳረሻውም ሳይከለክል የተወው ምንም ጉዳይ የለም።
ስለዚህም ሃይማኖቱን ያከበሩና ሥርዓቱንም የጠበቁት ከሰዎች ሁሉ እጅግ ደስተኛ፤ ራሳቸውን ስርዓት በማላበስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ፣ የመልካም ሥነ-ምግባርና የመልካም ስርዓት ባለቤት መሆን የቻሉት። ይህንን ደግሞ የቅርቡም የሩቅም ሰው የሚመሰክረው ጉዳይ ነው።
በሃይማኖታቸው ቸልተኛ የሆኑና ከቀጥተኛው መንገድ ያፈነገጡ ሙስሊሞች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቶ ብቻ መፍረድማ በምንም መልኩ ፍትህ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም እንደዛ ማድረጉ በራሱ ግፍ ነው።
በመጨረሻም ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ እስልምናን እንዲያውቁና ወደ እስልምናም እንዲገቡ ግብዣዬ ነው።
ወደ እስልምና ለመግባትም "ላ ኢላሀ ኢለላህ ሙሐመዱን ረሱሉላህ" ብሎ በአላህ አንድነትና በነብዩ ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኝነት ከመስከር ውጭ ሌላ ነገር የለውም።ከዚያም አላህ ግዴታ ያደረገበትን ሃይማኖቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን እውቀት ማወቅ ነው።ብዙ በተማረና ተግባራዊም ባደረገ ቁጥር ደስታውም እየጨመረና በጌታው ዘንድ ያለው ደረጃም ከፍ እያለ ይሄዳል።