Description
እስልምና በቁርኣን እና በነብያዊ ሓዲሥ በመጣው መሰረት ስለ ኢስላም አጠር ያለ መልዕክት
ሌሎች ትሩጓሜዎች 39
Topics
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
(ማስረጃ አልባ ቅጂ)
አጠር ባለ መልኩ እስልምናን ስለ ማስተዋወቅ፣ ስለ አሳሳቢ መሰረቶቹ፣ ስለ አስተምህሮቱ እንዲሁም ስለ መልካምነቱ መሰረታዊ ምንጮቹ ከሆኑት ቅዱስ ቁርኣን እና ነብያዊ ሓዲሥ በመመርኮዝ የሚዳስስ አሳሳቢ ፅሁፍ ሲሆን፤ ፅሁፉ ሙስሊምንም ይሁን ከሙስሊም ውጭ ያለውን ለአቅመ ሃላፊነት (አዳም ወይም ሄዋን) የደረሰ በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የሚገኘውን በየትኛውም መስክም ሁኔታም የሚገኝን ሁሉ የሚመለከት ፅሁፍ ነው።
1. እስልምና ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የተላከ ዘላለማዊ የሆነ አምላካዊ የአላህ መልዕክት ነው።
2. እስልምና ለተወስኑ ነገዶች ወይንም ህዝቦች ብቻ የሆነ ሃይማኖት ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ የሆነ የአላህ ሃይማኖት ነው።
3. እስልምና የአላህ ሰለት እና ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈንና የቀደምት ነብያቶች እና መልዕክተኞች ወደ ህዝቦቻቸው የተላኩበት ተልዕኮ ማሟያ የሆነ አምላካዊ ተልዕኮ ነው።
4. ነብያቶች ሁሉ የአላህ ሰላት እና ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈንና ሃይማኖታቸው አንድ ሲሆን መመሪያ ድንጋጌያቸው የተለያየ ነው።
5. እስልምና የሚጣራው፦ ኑሕ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ሱለይማን፣ ዳውድ፣ ዒሳ የአላህ ሰላት በእነርሱ ላይ ይስፈንና ~ሁሉም ነብያቶች ወደ ተጣሩበት ብቸኛ ጌታ፣ ፈጣሪ፣ ሲሳይ ለጋሽ፣ ሕይወት ሰጭ፣ ሕይወት ነሺ፣ ንጉሰ ነገስት፣ የጉዳዮችም አስተናባሪ ርህሩህ አዛኝ በሆነው አላህ ወደ ማመን ነው።
6. ጥራት ይገባውና ከፍ ያለው አላህ ፈጣሪ እና ለአምልኮም ብቸኛው ተገቢ የሆነ ከእርሱም ውጪ ሌላ ማንም አብሮት ሊመለክ የማይገባው ነው።
7. በፍጠረተ ዓለሙ ያለው የምናየውም የማናየውም ሁሉ ፈጣሪ አላህ ነው። ከእርሱም ውጭ ያለው ከፍጥረታቱ መካከል የሆነ ፍጡር ብቻ ነው። አላህ ሰማያትንና ምድርንም በሰባት ቀናት ፈጥሯል።
8. የላቀው እና ከፍ ያለው አላህ በንግስናውም ሆነ በመፍጠሩ፤ በማስተናበሩም ሆነ በአምልኮው ተጋሪ የለውም።
9. የላቀው እና ከፍ ያለው አላህ አልወለደም አልተወለደምም ብጤም ሆነ አምሳያም የለውም።
10. የላቀውና ከፍ ያለው አላህ ከፍጥረታቱ መካከል በአንዳችም ነገር ላይ የሚሰርፅ አልያም የሚዋሃድ አይደለም።
11. የላቀውና ከፍ ያለው አላህ ርህሩህ አዛኝ በመሆኑ መልዕክተኞችን ልኳል ኪታቦችንም አውርዷል።
12. ፍጥረታትን ሁሉ ከመቃብራቸው በማስነሳት እያንዳንዱን የሚተሳሰባቸው እጅግ በጣም አዛኙ እና ብቸኛው ጌታ አላህ ነው። እያንዳንዱን ግለሰብ ለሰራው በጎም ይሁን ክፉ ስራ ይመነዳዋል። አማኝ ሆኖ መልካም የሰራ ዘውታሪ ፀጋ ያለለት ሲሆን ከሃዲ ከሆነ እና መጥፎን ለስራ ደግሞ በአኺራ ታላቅ ቅጣት አለለት።
13. ከፍ ያለው አላህ አደምን ከፈጠረ በኋላ ዝርያዎቹ ከእርሱ በኋላ እንዲባዙ አደረገ። በመሆኑም የሰው ልጆች ሁሉ በመሰረታዊ ማንነታቸው አንዱ ዝርያ ከሌላኛው አንዱ ህዝብ ከሌላኛው በማይበላለጥበት መልኩ እኩል ናቸው።
14. እያንዳንዱ ልጅ በተፈጥሯዊ ሃይማኖት ላይ ሆኖ ነው የሚወለደው።
15. ማንኛውም ሰው ስህተት ላይ ሆኖ ወይም ስህተትን ወርሶ አይወለድም።
16. የሰው ልጆች የመፈጠራቸው ዓላማ አላህን በብቸኝነት ማምለክ ነው።
17. እስልምና የሰውልጆችን –ወንዶቹንም ሆነ ሴቶቹን- ክብርን አጎናፀፋቸው፤ ለተሟላ መብታቸውም ዋስትናውን አረጋገጠላቸው፤ በተቀሩት ምርጫዎች፣ ድርጊቶችም ሆኑ ክንውኖች ተጠያቂነትን አደረገባቸው፤ ራሱንም ይሁን ሌላን ለሚጎዱ ድርጊቶች ሁሉ የተጠያቂነት ኅላፊነት ጣለባቸው።
18. ወንዶችን እና ሴቶችን ከተጠያቂነት፣ ከምንዳም ሆነ ከቅጣት አንፃር እኩል አደጓል።
19. እስልምና ሴትን ልጅ አከበረ፤ ሴቶቹን የወንዶቹ ክፋይ አድርጎም ቆጠረ፤ ወንድ እስከቻለ ድረስ ለሴት ይለግሳት ዘንድ ግዴታን ጣለበት፤ በመሆኑም አባት የሴት ልጁን ወጪ የመቻል ግዴታ አለበት፤ እናትም ወጪዋን ለመቻል የደረሰ ወንድ ልጅ ካላት፤ ሚስትም ባሏ ወጪዋን ሊችሉ ግዴታ አለባቸው።
20. ሞት ብሎ ማለት ሙሉ በሙሉ አልቆ መጥፋት ማለት ሳይሆን ከስራ አለም ወደ ምንዳ አለም መሸጋገር ነው። ሞት አካልንም ሩሕንም የሚመለከት ነው። የሩሕ ሞት ስንል ግን ከአካል መለየቷን ማለታችን ነው። ከዚያም በእለተ ትንሳኤ ከተቀሰቀሱ በኋላ ሩሕ ወደ አካል ትመለሳለች። ሰው ከሞተ በኋላ ሩሑ ወደ ሌላ አካልም አትሸጋገርም ወደ ሌላም አካል አትሰርፅም።
21. እስልምና በታላላቅ የእምነት መሰረቶች ወደ ማመን ይጣራል። እነርሱም፦ በአላህ ማመን፤ በመላእክቶች ማመን፤ በአምላካዊ መጽሐፍት በነ ተውራት፣ ኢንጂል፣ በነ ዘቡር –ከመበረዛቸው በፊት- ማመን እንዲሁም በቁርኣን ማመን፤ የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁንና በሁሉም ነብያቶች እና መልዕክተኞች ማመን እንዲሁም በመደምደሚያቸው የነብያቶችም የሩሱሎችም መደምደሚያ በሆኑት የአላህ መልዕክተኛ ሙሐመድ ማመን፤ በመጨረሻው ቀን ማመን ፤ የዱንያ ህይወት ብቻ እንጂ ሌላ አለም የሌለ ቢሆን ኖሮ ህይወትም ሆነ ህልውና ጥርት ያለ ተላላነት በሆነ ነበር- በቀዷ(ውሳኔ)ና በቀደር ማመን ናቸው።
22 .ነብያቶች ከአላህ በሚያደርሱት ተልእኳቸው ጥብቆች ናቸው፤ ህሊና ጋ ከሚጋጭም ሆነ ጥሩ ስነምግባር ከማይቀበለውም ነገር ሁሉም የተጠበቁ ናቸው፤ የአላህን ትእዛዞች ለባርያዎቹ የማድረስ ኃላፊነት የተሰጣቸውም ነብያቶቹ ናቸው። ነብያቶች ለአላህ ብቻ ካሉት አምላካዊም ሆነ ጌታዊ ማንነት ድርሻ የላቸውም። ይልቅ እነርሱም እንደሌላው ሰው ሲሆኑ አላህ ተልእኮውን የሚገልፅላቸው ሰዎች ናቸው።
23. እስልምና በባለ ታላላቅ መሰረቶች አምልኮ አላህን በብቸኝነት ወደ ማምልከ ጥሪ ያደርጋል፤ እነኝህም፡ ሰላት፦ እርሷም መቆም፣ (ሩኩዕ) ማጎብደድ፣ በግንባር መደፋት (ሱጁድ) አላህን ማወደስና መማፀንንም ያካተተ ሲሆን በየለቱ እያንዳንዱ ግለሰብ አምስት ጊዜ የሚሰግዳት እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ያሉ ልዩነቶችንም የሚያስወግድ ሃብታሙም ሆነ ድሃው፣ መሪውም ሆነ ተመሪው በአንድ መስመር ገጥመው የሚሰግዱት ግዴታ ነው። ዘካ ማለት ደግሞ አላህ ባስቀመጠው ጥቂት የገደብ መጠን በዓመት አንድ ጊዜ ከሃብታም ንብረት ተቀንሶ ለድሃና ለመሳሰሉት የሚሰጥ ግዴታ ነው። ፆም ደግሞ በወርሃ ረመዷን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ፆምን ከሚያፈርሱ ነገሮች ታቅቦ መዋል ሲሆን ነፍስን፣ ፍላጎትንና ትእግስትን የሚያሰለጥን ነው። ሐጅ ማለት ደግሞ በሚችል ሰው ሁሉ ላይ በእድሜ (በሕይወት) አንድ ጊዜ በተከበረው መካ የሚገኘውን የአላህን ቤት መጎብኘት ሲሆን በዚህ በስርአተ_ ሐጅ ሁሉም ወደ ፈጣሪ በመቅጣጨት እኩል በመሆናቸው ልዩነቶች እና መኮፈሻዎች ሁሉ ይወገዳሉ።
24. ኢስላማዊ አምልኮ ከሚለይባቸው መለያዎች መካከል አፈፃፀም ሁኔታውን፤ ጊዜውን ብሎም ቅድመ_መስፈርቱን ሁሉ ያስቀመጠው አላህ፤ መልዕክቱን ያደረሱት ደግሞ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና መልእክተኛው መሆናቸው ነው። ከድሮ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በመጨመርም ሆነ በመቀነስ የማንም ጣልቃ ገብነት የለበትም። እነኝህ ከፍ ብለን የጠቀስናቸው ታላላቅ አምልኮዎችም ቢሆኑ ነብያቶችም ሁሉ የተጣሩባቸው አምልኮዎች ናቸው።
25. ለእስልምና የአላህ መልዕክተኛው ከኢስማዒል የኢብራሂም ልጅ ዝርያ የሆኑት ነብዩ ሙሐመድ የዐብደላህ ልጅ ናቸው። በመካ እ. ኣ. አ. በ 571 ተልከው እዛው ተልእኮው የተሰጣቸው ሲሆን ወደ መዲና ሂጅራ አድርገዋል (ተሰደዋል)። ህዝባቸውንም በጣኦታዊ ጉዳያቸው ላይ አላገዟቸው። ይልቅ ህዝባቸውን ያግዙ የነበሩት በታላላቅ ስራዎች ላይ ነበር። ከመላካቸውም በፊት ባማረ ታላቅ ስነምግባር ላይ ነበሩ፤ ህዝቦቻቸውም አልአሚን (ታማኙ) ይሏቸው ነበር፤ እድሜያቸውም አርባ አመት በሞላ ጊዜ አላህ መልዕክተኛ አድርጎ ላካቸውና በታላላቅ ተአምራቶችም አጠነከራቸው ይበልጥ ታላቁ (ተዓምር) የተከበረው ቁርኣን ነው። ይኸውም የቁርኣን ተአምርነት ከነብያቶች ተአምር ሁሉ እጅግ በጣም ታላቁ ተአምር ሲሆን ከነብያቶች ተአምር ሁሉ እስከዛሬ ድረስ የዘለቀውም ተአምር እሱው ነው። አላህ ለእርሳቸው ዲኑን ባሟላላቸው ጊዜ መልእክተኛውም ተልእኳቸውን በተሟላ መልኩ ያደረሱ ሆነው እድሜያቸው 63 አመት በሞላ ጊዜ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ከተማ መዲና ተቀበሩ። የአላህ መልእክተኛ ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የነብያቶችና የመልእክተኞችም መጨረሻ ሲሆኑ አላህ የሰው ልጆችን ሁሉ ከጣኦታዊ የክህደትና የድንቁርና ጨለማዎች ወደ ተውሒድና ኢማን ብርሃን ሊያወጡ ላካቸው። አላህም በእርሱ ፈቃድ ወደ እርሱ የሚጣሩ መሆናቸው መሰከረላቸው።
26. ነብዩ ሙሐመድ -የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን- ይዘውት የመጡት የእስልምና ድንጋጌ የአምላካዊ ተልእኮዎችና የጌታችን የአላህ ድንጋጌዎች መጨረሻ ነው። ይህም የሙሉነት ድንጋጌ ሲሆን በውስጡም የሰው ልጆች ዲናዊም ሆነ ዱንያዊ መስተካከል የያዘ ነው። ይህ ሸሪዓ በመጀመርያ ደረጃ የሰው ልጆችን ሃይማኖት፣ ደማቸውን፣ ንብረታቸውን፣ አእምሯቸውን፣ ዝርያቸውን ይጠብቅላቸዋል። የቀደሙት ሸሪዓዎች ከፊሉ ከፊሉን ሲሽር እንደ ነበረው ሁሉ የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሸሪዓም ቀደምት ድንጋጌዎችን ሁሉ የሚሽር ነው።
27. ጥራት የተገባውና ከፍ ያለው አላህ መልዕክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይዘውት ከመጡት ሃይማኖት ውጭ ሌላን ሃይማኖት አይቀበልም። በመሆኑም ከእስልምና ውጭ ያለን ሃይማኖት፥ ሃይማኖት አድርጎ የያዘን አላህ አይቀበለውም።
28. የተከበረው ቁርኣን ከፍ ያለው አላህ ለመልዕክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን በወሕይ (ራእይ) አማካኝነት ያወረደላቸው ኪታብ የአላህ ቃል ነው። የእርሱን አምሳያ ወይም የእርሱን አምሳያ አንዲት ምእራፍ እንኳ እንዲያመጡ አላህ የሰው ልጆችንም ይሁን አጋንንቶችን ሁሉ ያፎካከረበት ነው። ማፎካከሩ ዛሬም ድረስ ያለ ነው። ይህ ታላቁ ቁርኣን ብዙ እልፍ አእላፍ ሰዎችን የሚያሳስቡ በርካታ ጥያቄዎችን ይመልሳል። ይህ ታላቁ ቁርኣን የወረደበት በሆነው የዓረብኛ ቋንቋ የአንዲት ሆሄ (ፊደል) እንኳ መጨመር እና መቀነስ ሳይኖርበት እንደተጠበቀ ነው ያለው። ታትሞ የተሰራጨም ነው፤ ተዓምራዊ ሲሆን መቅራቱም ሆነ የተተረጎመውን ማንበቡ አስፈላጊ የሆነ ታላቅ መጽሐፍ ነው። ልክ የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ፈለግ፣ አስተምህሮትና ታሪካቸውም የተጠበቀ እና በታማኝ ዘጋቢዎች ሰንሰለት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እንዲሁም እሳቸው ሲናገሩበት በነበረው የዓረብኛ ቋንቋም የታተመ ብሎም ወደ በርካታ ቋንቋ የተተረጎመ እንደሆነው ሁሉ። የተከበረው ቁርኣን እና የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሱና ለዲነል ኢስላም ህግጋትና ድንጋጌዎች ብቸኞቹ ምንጮች ናቸው። የእስልምና ምንጩ ራሳቸውን ወደርሱ ከሚያስጠጉ ግለሰቦች ድርጊት ሳይሆን ከአምላካዊ ወሕይ (ራእይ) ነው የሚያዘው፤ እነርሱም የተከበረው ቁርኣን እና ነብያዊ ሱና ናቸው።
29. እስልምና ለወላጆች ሙስሊም እንኳ ባይሆኑ በጎ መዋልን ያዛል፤ ስለ ለጆች መልካም ስለመዋልም አደራ ያስተላልፋል።
30. እስልምና ከጠላት ጋር እንኳ ቢሆን በተግባርም ሆነ በንግግር ፍትሃዊ መሆንን ያዛል።
31. እስልምና ለፍጥረታቱ ሁሉ በጎ መዋልን የሚያዝ ሲሆን ወደ መልካም ስነ_ምግባርና ወደ በጎ ስራዎችም ጥሪ ያደርጋል።
32. እስልምና እንደ እውነተኝነት፣ አደራን መወጣት፣ ጥብቅነት፣ አይነ_አፋርነት፣ ጀግንነት፣ ለጋስነት፣ ቸርነት፣ የተቸገረን መርዳትና የወደመበትን መታደግ፣ የተራበን ማብላት፣ መልካም ጉርብትና፣ ዝምድናን መቀጠል፣ ለእንስሳት እንኳ ሳይቀር ማዘንን ወደ መሰሉ ምስጉን የሆኑ ስነ_ምግባሮች ሁሉ ጥሪ ያደርጋል።
33. ከሚጠጣም ሆነ ከሚበላ ነገር እስልምና ጥሩውን ፈቅዷል፤ ልቦናንም ሆነ አካልን እንዲሁም መኖሪያንም ንፁህ ማድረግን አዟል፤ የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈንና ነብያቶችን እንዳዘዙት ሁሉ፤ ጋብቻን ፈቅዷል፤ እነርሱም ጥሩን ነገር ሁሉ የሚያዙ ናቸውና።
34. እስልምና በአላህ ማጋራት፣ ክህደት፣ ጣኦት አምልኮ፣ በአላህ ላይ ያለ እውቀት መናገር፣ ልጅን መግደል፣ ክቡር የሆነችውን የሰውን ልጅ ነፍስ ማጥፋት፣ በምድር ላይ ማበላሸት፣ ድግምት፣ ግልጽም ይሁን ድብቅ ብልግና፣ ዝሙት፣ ግብረሶዶም፣ ወለድ መብላትንም ከልክሏል፣ የበከተን መብላት፣ ለጣኦታትና ለቅርፃ ቅርፁ ተብሎ የታረደን ስጋ መብላት፣ የአሳማ ስጋን መብላት እና ሌሎችም እርኩስና ቆሻሻን ነገሮች ሁሉ ከልክሏል፣ የየቲም (ወላጅ የሞተበት) ልጆችን ንብረት መብላት፣ ሚዛንና መለኪያን ማዛባት፣ ዝምድና መቁረጥን የመሰሉ የሐራም (እርም) ነገሮች ሁሉ መሰረት የሆኑትን ይከለክላል። ሁሉም ነብያቶችም እነዚህ የተዘረዘሩት የተከለከሉ ሓራም (እርም) መሆናቸው ላይ ይስማማሉ።
35. እስልምና እንደ ውሸት፣ ማታለል፣ መካድ፣ ክፋትን ማመርቀዝ፣ ምቀኝነት፣ መጥፎ ተንኮል፣ ስርቆት፣ ድንበር ማለፍንና ሰዎችን መበደልን ከመሰሉ የተወገዙ ስነ_ምግባሮችና ቆሻሻ (መጥፎ) ማንነቶች ሁሉ ይከለክላል።
36. እስልምና ወለድ፣ የሰዎች ጉዳት፣ መሸወድ (ማታለል)፣ ሰዎችን መበደል፣ ማጭበርበር ካለበትም ሆነ ማኅበራዊም ይሁን ህዝባዊ ወይንም ግለሰባዊ ጉዳት ወደ ማምጣት ሊያደርስ የሚችልን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ይከለክላል።
37. እስልምና የመጣው አእምሮን በመጠበቅ እና አስካሪ መጠጥ መጠጣትን ከመሰሉ አእምሮን ከሚያበላሹ ነገሮች በመከልከል ነው። እስልምና የአዕምሮንም ደረጃ ከፍ በማድረግ /የፍርድ ማብሰልሰያ አድርጎ ከአጉል እምነትም ሆነ ከጣዖት አምልኮ ጭንቅ ገላገለው። በመሆኑም በእስልምና አንዱን የማኅበረሰብ ክፍል ከሌላው የሚለዩ ምስጢሮች ወይም ፍርዶች የሉም፤ ሁሉም ፍርዶቹ እና ህጎቹ ጤናማ ከሆኑ አዕምሮዎችም ጋር የሚስማሙ ናቸው፤ እነሱም የፍትህና ጥበብ መሰረቶች ውጤት ጋ የገጠሙ ናቸው።
38. ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ተከታዮቻቸው በውስጣቸው ያሉትን ቅራኔዎች እና አዕምሯቸው የማይቀበሏቸውን ጉዳዮች ካልተረዱ የሃይማኖቱ አባቶች ሃይማኖትን ከምክንያት በላይ ነው ብለው ተከታዮቻቸውን ያታልላሉ። አዕምሮም ሀይማኖትን መረዳትና መገንዘብን ለመቻል እድሉ የለውም። እስልምና ሃይማኖቱን ለአእምሮ ጎዳና የሚያበራለት ብርሃን እንደሆነ አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን የሐሰት ሃይማኖቶች ግን ሰው አእምሮውን ትቶ እነሱን እንዲከተል ይፈልጋሉ። እስልምና ታድያ ሰው የነገሮችን እውነታ ባሉበት ተጨባጭ ያውቅ ዘንድ አዕምሮውን እንዲያነቃ ይፈልጋል።
39. እስልምና ትክክለኛ እውቀትን ያልቃል። ስሜትን ከመከተል የጠራ የሆነ ሳይንሳዊ ምርምርንም ያበረታታል። ስለ ራሳችንም ሆነ በዙሪያችን ስላለው ፍጥረተ_ዓለም (ከውን) በተመለከተ እንድናስተነትን ጥሪ ያደርጋል። በመሆኑም ትክክለኛ የሳይንስ ምርምር ውጤቶች ከእስልምና ጋር አይጋጩም።
40. በአላህ አምነው ለታዘዙትና መልእክተኞቹንም የአላህ ሰላትና ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈን እውነት ብለው የተቀበሉትን ካልሆነ በቀር፥ አላህ ከማንም ስራውንም አይቀበለውም፤ ለመልካም ስራውም ኣኺራ (በዘላለማዊው ዓለም) ላይ አይመነዳውም። የደነገገውንም ካልሆነ በቀር የትኛውንም አምልኮ ተግባር አይቀበልም። የሰው ልጅ በአላህ ከካደ በኋላ አላህ መልካምን ምንዳ ይሰጠዋል ተብሎ እንዴት ይታሰባል?! ማንኛውም ሰውም ቢሆን በሁሉም ነብያቶች ብሎም በነብዩ ሙሐመድም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የአላህ መልእክተኝነት አምኖ ካልተገኘ አላህ እምነቱን አይቀበለውም።
41. የሁሉም መለኮታዊ ተልእኮዎች ግብ፡ እውነተኛው ሃይማኖት ወደ ሰው ልጅ እንዲሰርፅ ብሎም ለዓለማት ጌታ አላህ ንጹሕ ባርያ ይሆን ዘንድ፤ የሰው ልጅን ከጎጂ ባህል ወይም ከአጉል እምነት ወይንም ከቁሳዊ ባርነት ነፃ ያውጣው ዘንድ ነው። ይኸውና እስልምና የሰዎችን ፍፁምነትንም አይሞግትም ካላቸው ሰብአዊ ደረጃ በላይ አንስቶ ጌቶች እና አማልክት አያደርጋቸውም።
42. አላህ በእስልምና ንስሀን (ተውባን) ደንግጓል፡ ይህም፦ አንድ ሰው ባጠፋ ግዜ ወደ ጌታው መመለሱ እና ኃጢአቱን መተው ነው፤ እስልምና ከሱ በፊት የነበሩትን ኃጢአቶች ያጠፋል (ያስምራል)፤ ንስሐም ከዚህ በፊት የነበሩትን ኃጢአቶች ሁሉ ይሰርዛል፤ ለዚህም ማንም ኋጢአቱን በሰው ፊት መናዘዝ አያስፈልገውም።
43. በእስልምና በሰው እና በአላህ መካከል ያለው ቁርኝት ቀጥተኛ ነው። በአንተና በአላህ መካከል ማንም አማላጅ አያስፈልግህም። የእስልምና ሃይማኖት እኛ የሰው ልጆችን አማልክት ወይንም በጌትነቱ ወይም በአምላክነቱ ለአላህ ተጋሪ ከማድረግ ይከለክለናል።
44. በዚህ ጽሁፍ መጨረሻ ላይ ማውሳት የምንፈልገው ነገር ቢኖር፦ ሰዎች በተለያዩ ጊዜዎች፣ ብሄሮችና ሀገሮች መሆናቸውን እናስተውላለን፤ ኧረ እንደውም መላው የሰው ልጅ ማህበረሰብ በሀሳቡ እና በዓላማው የተለያየ በአከባቢው ሆነ በድርጊቱም የተለያየ በመሆኑ አንድ የሚያደርግ ሥርዓት እና ጥበቃን የሚያደርግለት ገዥ ወደ ጥሩ የሚመራው መመሪያ ጋር ግዴታ ያስፈልገዋል። የአላህ የአላህ ሰላትና ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈንና የተከበሩት የአላህ መልእክተኞችም ከአላህ -ሱብሓነሁ ወተዓላ- በሚወርድላቸው ወሕይ (መለኮታዊ ራእይ) በአላህ ሸሪዓ በማሰባብሰብ፣ በሰዎች መካከል በእውነት በመፍረድ ሰዎችን ወደ መልካምና ቀና ጉዳና የመምራት ኃላፊነትን ተሸክመው ነበር። ሰዎች ለነኝህ የአላህ መልእክተኞች ተልእኮ ባላቸው ምላሽ ሰጭነት እንዲሁም ለመለኮታዊው ጥሪም ባላቸው የጊዜ ቅርበትም ልክ ሁኔታቸው ይስተካከል ነበር። የላቀው አላህ መልእክተኛውን ሙሐመድን የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን በመላክ ለሰው ልጆች የሚያስተላልፈውን ተልእኮ ደመደመና ለነብያችን ሙሐመድ ተልእኮም ዘለቄታን ፃፈለት (ዘውታሪ እንዲሆን ደነገ)፤ ለሰው ልጆችም ምራቻ፣ እዝነት፣ ብርሃን፣ ወደ ላቀው አላህ የሚመራም ቅን ፈለግ አደረገው።
45. ስለዚህም የሰው ልጅ ሆይ! ከአጉል ባህልና ከልምድ እንዲሁም ከድንቁርና በመላቀቅ እስልምናን ተቀብለህ በሐቀኝነት ለአላህ እንድትቆም ከሞትክም በኋላ ወደ ጌታህ ተመላሽ መሆንህን እንድታውቅ፤ ራስህንም በዙሪያህ ያለውንም አድማስ እንድትመለከት አደራ እያልኩ እጋብዝሃለሁ። ያኔ በሃይማኖታዊም በዓለማዊም ጉዳይህ ደስተኛ ትሆናለህ። ወደ እስልምና ሃይማኖት ለመግባት ከፈለጉም "ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለና ሙሐመድም የአላህ መልእክተኛ እንደሆኑ" ለመመስከር "ላ ኢላሃ ኢለላህ ሙሐመዱን ረሱሉላህ" ብሎ መመስከር ብቻ ነው ያለብዎት። ይህችን የምስክርነት ቃል ከሰጡ ሙስሊም ሆነዋል። ከዚህ በኋላ አላህ በደነገገው መልኩ ሰላትንም እየሰገዱ፣ ፆሞን እየፆሙ፣ ከቻሉም ሐጅ በማድረግ አላህን ማምለክ ላይ አደራ።
የቀን 19-11-1441 ቅጂ
ጸሐፊ መምህር ዶክተር ሙሐመድ ቢን ዐብደላህ አስሱሐይሚ
በኢስላማዊ አስተምህሮ ክፍል የቀድሞ የዓቂዳ አስተማሪ
መሊክ ሰዑድ ዩኒቨርሲቲ የተርቢያ ዲፓርትመንት (ኮሌጅ)
በሪያድ ሳዑዲ ዓረቢያ