Description
ለሰለሙ ጠቃሚ መመሪያ
ሌሎች ትሩጓሜዎች 49
አዘጋጅ
ሙሐመድ አሽ ሺህሪይ
1441-2020
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና ሁሉ ለአላህ የተገባ ነው፤ እናመሰግነዋለን፤ እርዳታንም እንጠይቀዋለን፤ ምህረትንም እንለምነዋለን፤ ከነፍሶቻችን ክፋትና ከመጥፎ ሥራችንም በእርሱ እንጠበቃለን።አላህ የመራውን የሚያጠመው የለም፤ ያጠመመውን ደግሞ የሚመራው የለም።ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚገዙት አምላክ አለመኖሩን፣ብቸኛና ተጋሪ የሌለው መሆኑን እመስክራለሁ፤ ሙሐመድም መልእክተኛው እና ባሪያው መሆናቸውንም እመስከራለሁ።
ከዚህ በመቀጠል፦
አላህ የሰው ልጆችን ከፈጠራቸው በርካታ ፍጥረታት በላይ አስበልጧቸዋል። ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَلَقَدْ كَرَّمْنَا بَنِي آدَمَ﴾ "የአደምንም ልጅ በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው።"(አል-ኢስራእ፡ 70)አላህ የዚህን ሙስሊም ኡማ (ህዝብ) ክብር ከነቢያቶች ሁሉ ምርጥ የሆኑትን ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመላክ ፣ ከመጽሐፍት ሁሉ ምርጥ የሆነውን ቁርኣን በማውረድ እና ከሃይማኖቶች ሁሉ ታላቅ የሆነውን የእስልምናን ሃይማኖት ድንጋጌ ወዶላቸው አክብሮቱን ላቅ አደረገላቸው።﴿كُنْتُمْ خَيْرَ أُمَّةٍ أُخْرِجَتْ لِلنَّاسِ تَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَتَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنْكَرِ وَتُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَلَوْ آمَنَ أَهْلُ الْكِتَابِ لَكَانَ خَيْرًا لَهُمْ مِنْهُمُ الْمُؤْمِنُونَ وَأَكْثَرُهُمُ الْفَاسِقُونَ﴾ "ለሰዎች ከተገለጸች ሕዝብ ሁሉ በላጭ ኾናችሁ በጽድቅ ነገር ታዛላችሁ፤ ከመጥፎም ነገር ታዛላችሁ፤ በአላህም (አንድነት) ታምናላችሁ፡፡ የመጽሐፉም ሰዎች ባመኑ ኖሮ ለነርሱ የተሻለ በኾነ ነበር፡፡ ከነርሱ አማኞች አሉ፡፡ አብዛኞቻቸው ግን አመጸኞች ናቸው፡፡"[አሊ-ዒምራን፡ 110]የበላይ የሆነው አላህ ለሰው ልጅ ከዋለላቸው ታላላቅ ፀጋዎች መካከል ወደ እስልምና ሃይማኖት መምራቱ ፣ በእርሱም ላይ ፅናት መለገሱ እና ህግጋቶቹን እና ድንጋጌዎቹን እንዲፈጽም ማድረጉ ይገኝበታል። በዚህች መጠኗ ትንሽ ይዘቷ ግን ትልቅ በሆነች መጽሐፍ አዲስ ሰለምቴ የሆነ ሙስሊም የዚህን ታላቅ ሃይማኖት ጥቅል አስተምህሮንና የእስልምናን መሰረታዊ ነገሮች አጠር ባለ መልኩ ይማርበታል። አንዴ ከተረዳቸው እና ህግጋቱንም ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ ስለ ጌታው አላህ፣ ስለ ነቢዩ ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና ስለ ሃይማኖቱ እስልምና ያለውን ዕውቀት የበለጠ ለመጨመር ፍለጋውን ይቀጥላል። በዚህም አላህን በዕውቀትና በማስረጃ ላይ ሆኖ ማምለክ ይችላል፤ ልቡ ይረጋጋል፣ ወደ አላህ በአምልኮ በመቃረብ እና የነብዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሱና (ፈለግ) በመከተልም እምነቱ እየጨመረ ይሄዳል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ባሉት ቃላት ሁሉ በረካ እንዲያደርግ፤ በእርሷም ኢስላምን እና ሙስሊሞችን የሚጠቅም ሊያደርግ ዘንድ፤ የእርሱ ፊት ብቻ ተፈልጎበት የተሠራ እና ምንዳውም በሕይወት ላሉም ሆነ ለሞቱ ሙስሊሞች ሁሉ እንዲያደርገው ከፍ ያለውን አላህ ብቻ እለምነዋለሁ፡፡
ምስጋና ለአላህ ይገባው፤ የዓለማት ጌታ ለሆነው፤ እንዲሁም እዝነትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ ላይ እና ቤተሰቡ እንዲሁም በባልደረቦቹ ላይ ይውረድ
ሙሐመድ ቢን አሽ'ሸይባህ አሽ ሺህሪ
12/11/1441ሒ
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿يَا أَيُّهَا النَّاسُ اعْبُدُوا رَبَّكُمُ الَّذِي خَلَقَكُمْ وَالَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ﴾ እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡(አል በቀራ፡ 21)ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿هُوَ اللَّهُ الَّذِي لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ﴾ "እርሱ አላህ ነው፤ ያ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ።"(አል ሐሽር፡ 22)ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ﴾ "የሚመስለው ምንም ነገር የለም እርሱ ሰሚ ተመልካች ነው።"(አሽ ሹራ፡ 11)
አላህ የእኔም ጌታየ የሁሉ ነገርም ጌታው ነው፤ የሁሉም ንጉስ (ባለቤት) ፣ የሁሉም ፈጣሪ ፣ የሁሉም ሲሳይ ለጋሽ እና የሁሉ ነገርም አስተናባሪ ነው።
አምልኮ (ዒባዳ) በብቸኝነት የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፤ ከእርሱም ውጭ ሌላ ጌታ የለም፤ ከእርሱም ውጪ ሌላ እውነተኛ አምላክ የለም።
አላህ ለራሱ ያፀደቀውና ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ለአላህ ያፀደቋቸው እጅግ ውብ የሆኑ ስሞች እና ምሉዕ የሆኑ ባህሪያት አሉት። እነዚህም የሙሉነት (የፍጽምነት) እና የውበት ጫፍ የደረሱ ናቸው። እርሱን የሚመስለው ምንም የለም፤ እርሱ ሰሚ ተመልካችም ነው።
ከአላህ እጅግ ውብ የሆኑ ስሞች መካከል፦
አር‐ረዛቅ (ሲሳይን ሰጪ/ለጋሽ)፣ አር‐ረሕማን (እጅግ በጣም አዛኝ)፣ አል‐ቀዲር (ሁሉን ቻይ የሆነ)፣ አል‐መሊክ (የሁሉም ንጉስ)፣ አስ‐ሰሚዕ (ሁሉን ሰሚ)፣ አስ‐ሰላም (ከእንከን ሁሉ ነፃ የሆነ ፍፁም፤ የሰላም ባለቤት)፣ አል‐በሲር (ሁሉን ተመልካች)፣ አል‐ወኪል (አስተዳዳሪው፣ የሁሉም ጉዳይ ባለቤት፤ የፍጡሩ ሁሉ ተወካይ)፣ አል‐ኻሊቅ (የሁሉም ፈጣሪ)፣ አል‐ለጢፍ (ውስጠ ዓዋቂ)፣ አልካፊ (ለሁሉም የሚበቃ)፣ አል‐ገፉር (መሃሪ)።
አር‐ረዛቅ (ለጋሽ ሲሳይን ሰጪ) ፦ ለባሮቹ ለልባቸውም ለአካላቸውም የሚያስፈልጋቸውን ሲሳይ በመስጠት ላይ ሙሉ አቅሙም ኃላፊነቱም ያለው።
አር‐ረሕማን (እጅግ በጣም አዛኝ) ፦ እጅግ በጣም ሰፊ፣ ሁሉን ነገር ያካበበና የታላቅ እዝነት ባለቤት የሆነ።
አል‐ቀዲር (ሁሉን ቻይ የሆነ)፦ ድካምም ሆነ መሳን የማያጋጥመው የተሟላ ችሎታ ባለቤት የሆነ።
አል‐መሊክ (ንጉስ) ፦በታላቅነት፣ በአሸናፊነት እና በአስተናባሪነት ባህሪያት የሚገለፅ፤ ሁሉንም ነገር በባለቤትነት የሚመራ እና የሚያስተናብር ነው።
አስ‐ሰሚዕ (ሁሉን ሰሚ) ፦ ምስጢሩንም ሆነ ይፋ የወጣውን ሁሉ የሚሰማ።
አስ‐ሰላም (ከእንከን ሁሉ ነፃ የሆነ ፍፁም፤ የሰላም ባለቤት)፦ ከማንኛውም ዓይነት ጉድለት፣ እንከንና ነውር ሁሉ የጸዳ ፍጹም የሆነ።
አል‐በሲር (ሁሉን ተመልካች) ፦ እይታው ትንሽንም ይሁን ደቃቅ እንኳ ሳያስቀር ሁሉንም ነገር የሚመለከት፤ በውስጣቸው የተደበቀን ሁሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ውስጥ ዓዋቂ ሁሉንም ነገር የማይት ችሎታ ያለው እይታ ባለቤት የሆነ።
አል‐ወኪል (አስተዳዳሪው፣ የሁሉም ጉዳይ ባለቤት፤ የፍጡሩ ሁሉ ተወካይ) ፦ የፍጥረታቱ ሲሳይ ባለ ሙሉ ኃላፊነት፣ ጉዳዮቻቸውን በሚበጃቸው መልኩ የሚያስተናብር፤ በእርሱ ለሚያምኑና እርሱን ለሚፈሩ እንዲሁም ወዳጆቹ ጉዳያቸውን የሚያመቻች፣ ለጉዳያቸው በቂያቸው የሆነ።
አል‐ኻሊቅ (የሁሉም ፈጣሪ) ፦ ቀዳሚ አምሳያ በሌለበት ሁኔታ (ያለ ቅድመ አምሳያ) ነገሮችን ፈጥሮ ህልውና የሰጣቸው።
አል‐ለጢፍ (በርኅራኄው ረቂቁ) ፦ ባሮቹን የሚያከብር፣ የሚራራላቸው እና ልመናቸውንም ተቀብሎ ምላሽ የሚሰጣቸው።
አል‐ካፊ (ለሁሉም በቂ)፦ ያ ባሮቹ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ በቂያቸው የሆነ፤ በእርዳታውም ከእርሱ ውጪ ካሉት ሁሉ የሚብቃቁበት ወይም የእርሱ እርዳታ ከሌሎች የሚያብቃቃ።
አል‐ገፉር (ይቅር ባይ)፦ ባሮቹን ከኃጢኣታቸው መዘዝ እና ቅጣት የሚጠብቃቸው።
አንድ ሙስሊም የአላህን ድንቅ ፍጥረታት እና ነገራቶችንም ለባሮቹ እንዴት እንዳገራቸው ያሰላስላል። ሁሉም ፍጡራን ታዳጊዎቻቸው አድገው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ የዚህ አንዱ መገለጫ ነው። ፈጥሮ ለሚራራላቸው አምላክ ጥራት ተገባው። ከርህሩህነቱ መገለጫዎች መካከል ሙሉ በሙሉ ደካማ ከመሆናቸውም ጋር እነርሱን የሚረዳ እና ሁኔታቸውንም የሚያስተካክል መሆኑ ተጠቃሽ ነው።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِنْ أَنْفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُمْ بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَحِيمٌ﴾ "ከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የኾነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ።"(አትተውባ፡128)ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلا رَحْمَةً لِلْعَالَمِينَ﴾ "(ሙሐመድ ሆይ!) ለዓለማትም እዝነት አድርገን እንጅ አልላክንህም።"[አል-አንቢያእ: 107]
ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የእዝነቱ ነብይ
ስማቸው ሙሐመድ ኢብን ዐብደላህ ይባላሉ፤ የነብያትም የመልእክተኞችም መደምደሚያ ናቸው። አላህ የእስልምናን ሃይማኖት ያስተምሩ ዘንድ ወደ ሰው ልጆች ሁሉ ላካቸው፤ ሰዎችን ወደ መልካም ነገር ያመላክቱ ዘንድ በተለይም ታላቅ የሆነውን የአላህ ብቸኛ ተመላኪነት ተውሒድ እንዲያስተምሩ እንዲሁም ከመጥፎ ነገሮች ሁሉ እንዲከለክሏቸው በተለይም ከባድ ከሆነው ወንጀል ሺርክ እንዲያስጠነቅቁ ነው የላካቸው።
ያዘዙትን መታዘዝ ፣ የተናገሩትን እውነት ብሎ ማመንና መቀበል ፣ ከከለከሉትና ካስጠነቀቁት ነገር መራቅ ፣ አላህን እርሳቸው ባስተማሩትና በደነገጉት መልኩ ብቻ ማምለክ ግዴታ ነው።
እርሳቸውም ይሁን ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ነብያት ሁሉ ተልዕኳቸው የነበረው አላህን ያለ ምንም ተጋሪ በብቸኝነት ወደ ማምለክ ጥሪ ማድረግ ነው።
ከነቢዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ባህሪያት መካከል፡-
እውነተኝነት፣ ርህራሄ፣ ቻይነት፣ ታጋሽነት፣ ጀግንነት፣ ቸርነት፣ መልካም ስነምግባር፣ ፍትሃዊነት፣ ትህትና እና ይቅር ባይነት (ከብዙ በጥቂቱ ናቸው)።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿ يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَكُم بُرْهَانٌ مِّن رَّبِّكُمْ وَأَنزَلْنَا إِلَيْكُمْ نُورًا مُّبِينًا﴾ "እናንተ ሰዎች ሆይ! ከጌታችሁ ዘንድ በእርግጥ አስረጅ መጣላችሁ፤ ወደእናንተም ገላጭ የሆነን ብርሃን (ቁርኣንን) አወረድን።"[አን-ኒሳእ: 174]
የተከበረው ቁርአን ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሰዎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ሊያወጡበትና ወደ ቀጥተኛው መንገድም ሊመሩበት ዘንድ የወረደላቸው የአላህ ቃል ነው።
ያነበበው ሰው ታላቅ ምንዳ ያገኝበታል፤ ትዕዛዛቱን የፈፀመ ደግሞ ቅኑን መንገድ ይከተላል።
የአላህ መልዕክተኛ ሰላትና ሰላም በእርሳቸዉ ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፦(እስልምና በአምስት (ማዕዘናት) ላይ ተገንብቷል፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድ የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን መመስከር፣ ሶላትን ደንቡንና ሥርዓቱን ጠብቆ መስገድ፣ ዘካ መስጠት፣ የረመዳንን ወር መጾም እና ሐጅ ማድረግ (የአላህን ቤት መጎብኘት))።
የእስልምና ማዕዘናት ማንኛውም ሙስሊም ሊፈፅማቸው የሚገቡ የአምልኮ ተግባራት ናቸው። የእነዚህ ማዕዘናት ግዴታነት ካላመነ እና እና ሁሉንም ካልተቀበለ በስተቀር የአንድ ሰው እስልምና ተቀባይነት አይኖረውም። ምክንያቱም እስልምና የታነፀው በእነርሱ ነውና፤ ለዚህም ነው የእስልምና ምሰሶዎች (ማዕዘናት) ተብለው የተሰየሙት።
እነዚህም ማዕዘናት የሚከተሉት ናቸው፦
የመጀመሪያው ማዕዘን፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ሙሐመድም የአላህ መልዕክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿فَاعْلَمْ أَنَّهُ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ﴾ "እነሆ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እወቅ።"(ሙሐመድ፡ 19)ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿لَقَدْ جَاءكُمْ رَسُولٌ مِّنْ أَنفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُم بِالْمُؤْمِنِينَ رَؤُوفٌ رَّحِيمٌ﴾ "ከጎሳችሁ የሆነ ችግራችሁ በእርሱ ላይ ጽኑ የሆነ፣ በእናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ፣ በምእምናን (ላይ) ርኅሩኅ አዛኝ የሆነ መልክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡"(አትተውባ፡128)
ላኢላሃ ኢለሏህ ማለት፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም ማለት ነው።
ሙሐመደን ረሱለሏህ ማለት ደግሞ፦ ያዘዙትን መታዘዝ ፣ የተናገሩትን እውነት ብሎ መቀበል ፣ የከለከሉትን እና ያስጠነቀቁቱን ነገር መራቅ እንዲሁም አላህን እርሳቸው በደነገጉት (ባስተማሩት) መልኩ ማምለክ ነው።
ሁለተኛው ማዕዘን፦ ሰላትን በአግባቡ መስገድ
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ﴾ "ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ።"(አል በቀራ፡ 110)
ሶላትን መስገድ ማለት፦ ሶላትን አላህ በደነገገው እና መልእክተኛው ሙሐመድ (የአላህ ሰላት እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ባስተማሩት መንገድ መስገድ ነው።
ሦስተኛ ማዕዘን፦ ዘካ መስጠት።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَآتُوا الزَّكَاةَ﴾ "ዘካንም ስጡ።"(አል በቀራ፡ 110)
ከፍ ያለው አምላክ አላህ ዘካን የአንድ ሙስሊምን እምነት እውነተኝነት መፈተኛ እንዲሆን፣ አላህ ስለዋለለት የገንዘብ ፀጋ ማመስገኛ እንዲሆንና እና ለድሆችና ለችግረኞችም ድጋፍ ሊሆን ዘንድ ግዴታ አድርጎታል።
የዘካ ግዴታን መወጣት የሚቻለው ለሚገባቸው በመስጠት ነው።
ይህም የተወሰነ መጠን ላይ ከደረሰ ገንዘብ ውስጥ የሚወጣ የተወሰነ የግዴታ መጠን ነው፤ አላህ በተከበረው ቁርኣን ውስጥ ለጠቀሳቸው ስምንት ዓይነት ምድቦች የሚሰጥ ነው፤ ከነዚህም መካከል ድሆች እና ችግረኞች ይገኙበታል።
በአፈፃፀሙ ሂደት ላይ እዝነት እና ደግነትን መላበስ፣ የሙስሊሙን ስነ-ምግባር እና ሀብት ማጥራት፣ የድሆችን እና የችግረኞችን ነፍስ ማርካት፣ በህዝበ ሙስሊሙ መካከል ያለውን የፍቅር እና የወንድማማችነት ትስስር ማጠናከርን ይዟል። በዚህም ምክንያት መልካም የሆነ ሙስሊም ለሌሎች ሰዎች የሚሰጠውን ደስታ በማሰብ ዘካን እርካታ እየተሰማውና በማውጣቱ ደስተኛ እየሆነ ነው የሚሰጠው።
የዘካው መጠን ከወርቅ፣ ከብር፣ ከገንዘብ ኖቶችና ለትርፍ ከተዘጋጁ ለግዥና ሽያጭ የተቀመጡ የንግድ ዕቃዎች ገንዘብ ውስጥ 2.5% ነው። (ዘካ የሚወጣውም ንብረቱ) ለዘካ የተወሰነለት መጠን ላይ ደርሶ (በጨረቃ አቆጣጠር) አንድ ዓመት ከሞላው ነው።
አብዛኛውን የዓመቱን ጊዜ ባለቤቱ ሳይመግባቸው ከመሬቱ ሳር የሚግጡ የሆኑ ለዘካ በተወሰነው መጠን ብዛት የደረሱ እንስሳት (ግመል፣ ላም እና በግ) ያለው ሰው ዘካ ማውጣት ግዴታ እንደሚሆንበት ሁሉ ማለት ነው።
እንዲሁም የተወሰነ መጠን ላይ የደረሰ ከምድር የሚገኝ እህል እና ፍራፍሬ እንዲሁም ማዕድን እና ከምድር ውስጥ ተቀብሮ ከተጋኘ ድልብ ላይም ዘካህ ግዴታ ነው።
አራተኛ ማዕዘን፦ የረመዳንን ወር መፆም
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا كُتِبَ عَلَيْكُمُ الصِّيَامُ كَمَا كُتِبَ عَلَى الَّذِينَ مِنْ قَبْلِكُمْ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ﴾ "እናንተ ያመናችሁ ሆይ ጾም በነዚያ ከናንተ በፊት በነበሩት (ሕዝቦች) ላይ እንደ ተጻፈ በናንተም ላይ ተጻፈ (ተደነባ) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና፡፡"(አል በቀራ፡ 110)
ረመዳን፡- በሂጅሪያ የዘመን አቆጣጠር የዓመቱ ዘጠነኛው ወር ሲሆን ሙስሊሞች ዘንድ የተከበረና የተቀደሰ ወር ነው፤ ከቀሪዎቹ የዓመቱ ወራት የተለየ ደረጃ ያለው ወር ነው፤ ሙሉውን ወር መፆም ከአምስቱ የኢስላም መሰረቶች (ማዕዘናት) መካከል አንዱ ነው።
የረመዳን ጾም ማለት፡- የተባረከውን የረመዳን ወር በቆየባቸው ቀናት ውስጥ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከግብረ ስጋ ግንኙነት እና ሌሎች ፆምን ከሚያበላሹ ነገሮች በመከልከል ከጎህ መቅደድ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሙሉ ቀኑን ከፍ ያለውን አምላክ አላህ ማምለክ ነው።
አምስተኛው ማዕዘን፡- ሐጅ ማድረግ የተከበረውን አላህን ቤት መጎብኘት
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَلِلَّهِ عَلَى النَّاسِ حِجُّ الْبَيْتِ مَنِ اسْتَطَاعَ إِلَيْهِ سَبِيلًا﴾ "ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መሄድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው።"[አሊ-ዒምራን፡ 97]ሐጅ ማድረግ ወጪውን ለቻለ ሰው በሕይወቱ አንድ ጊዜ ብቻ ግዴታ ነው። ይሀውም ወደ ተከበረው ቤት እና መካ አል-ሙከረማህ ወደሚገኙ ቅዱሳን ስፍራዎች በመሄድ የተወሰኑ የአምልኮ ተግባራትን በተወሰነ ጊዜ መፈፀም ነው። ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና ከእርሳቸውም በፊት የነበሩ ነብያትም ሐጅ አድርገዋል። እንዲሁም አላህ ኢብራሂምን ሰዎችን ወደ ሐጅ ጉዞ እንዲያደርጉ እንዲያውጁ አዟቸዋል። ይህንንም አላህ በተከበረው ቃሉ ቁርኣን ነግሮናል፦﴿وَأَذِّنْ فِي النَّاسِ بِالْحَجِّ يَأْتُوكَ رِجَالًا وَعَلَى كُلِّ ضَامِرٍ يَأْتِينَ مِنْ كُلِّ فَجٍّ عَمِيقٍ﴾ "(አልነውም)፡- በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትዕዛዝ ጥራ፡፡ እግረኞች ከየሩቅ መንገድ በሚመጡ ከሲታ ግመሎችም ሁሉ ላይ ሆነው ይመጡሃልና፡፡"[አል-ሐጅ: 27]
የአላህ መልዕክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለ ኢማን (እምነት) ተጠይቀው እንዲህ ሲሉ መልሰዋል፦(በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን ማመን እና በቀደር መልካምም ሆነ መጥፎ በሆነ (የአላህ ቅድመ ውሳኔ) ማመን ነው)።የእምነት ማዕዘናት በልብ ከሚፈፀሙ የአምልኮ ተግባራት የሚመደቡ ሲሆኑ፤ በእነርሱ ማመን በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው፤ በእነርሱ እስካላመነ ድረስ የአንድ ሰው እስልምና ትክለኛ አይሆንም፤ ለዚህም ነው የእምነት ማዕዘናት ተብለው የተሰየሙት።በኢማን ማዕዘናት እና በኢስላም ማዕዘናት መካከል ያለው ልዩነት፦ የኢስላም ማዕዘናት አንድ ሰው በአካሉ የሚፈጽማቸው በግልፅ የሚታዩ ተግባራት ሲሆኑ ለምሳሌ ሁለቱን የምስክርነት ቃላት በአንደበት መመስከር፣ ሶላት እና ዘካን መጥቀስ ይቻላል። የኢማን ማዕዘናት ደግሞ በልብ የሚፈፀሙ ተግባራት ሲሆኑ አንድ ሰው በልቡ የሚሠራቸው ናቸው። ለምሳሌ በአላህ፣ በመጽሐፍቱ እና በመልዕክተኞቹ ማመንን መጥቀስ ይቻላል።
የኢማን (እምነት) ፅንሰ-ሀሳብ እና ትርጉሙ፡- ኢማን ማለት በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልዕክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን እና መልካምም ይሁን መጥፎ በቀደር በቁርጠኝነት በልብ ማመን፤ መልእክተኛው ይዘው የመጡትን (አስተምህሮ) ሁሉ መከተል እና ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም የላኢላሃ ኢለላህ (ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ አምላክ አለመኖሩን) በምላስ መመስከር ፣ ቁርኣን ማንበብ፣ ሱብሐነላህ (ጥራት ለአላህ ተገባው) ላኢላሃ ኢለላህ ማለት እና አላህን ማወደስ መሰል ቃላቶችን በአንደበት መናገርን ሁሉ የሚያካትት ነው።
በጉልህ አካል ከሚሠሩት መካከል፡- እንደ ሶላት፣ ሐጅ፣ ጾም... የሚጠቀሱ ሲሆን በውስጣዊ አካል ከሚሰሩት መካከል ደግሞ አላህን መውደድና መፍራት፣ በእርሱ መመካትና ለእርሱ መታመን (ኢኽላስ) መሰል የልቦና ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የዘርፉ ሊቃውንቶች (ዑለማዎች) ኢማንን ባጭሩ ሲገልፁት፡- በልብ የሚታመን፣ በምላስ (በአንደበት) የሚነገር፣ በአካል ክፍሎች የሚተገበር አላህን በመታዘዝ የሚጨምር እና አላህን በማመፅ (ባለመታዘዝ) ደግሞ የሚቀንስ ነው ይላሉ።
የመጀመሪያው ማዕዘን፦ በአላህ ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ آمَنُوا بِاللَّهِ﴾ "ምእመናን ማለት እነዚያ በአላህና በመልክተኛው ያመኑት ናቸው።"(አንኑር፡ 62)
በአላህ ማመን በጌትነቱ፣ በአምላክነቱ፣ በስምና ባህሪያቱ አላህን ብቸኛ ማድረግን ያጠቃልላል። እንዲሁም የሚከተሉትን ያጠቃልላል፦
አላህ መኖሩን ማመን።
የበላይና ጥራት የተገባው በሆነው አላህ ጌትነት ማመን፤ እርሱ የነገሩ ሁሉ ባለቤት፣ ፈጣሪ፣ ሲሳይ ሰጪና አስተናባሪ መሆኑን ማመን።
በአምላክነቱ ማመን፤ አላህ በብቸኝነት ሊመለክ የሚገባው መሆኑን ፤ የአምልኮ ተግባራትን ያለ አንዳች ተጋሪ ለእርሱ ብቻ ማድረግ፤ ከእነርሱም መካከል ሶላት፣ ዱዓ (ልመና)፣ ስለት፣ እርድ፣ እርዳታን መፈለግ፣ ጥበቃን መፈለግ እና ሌሎችን ዒባዳዎች ሁሉ (ለአላህ ብቻ ማድረግ)።
አላህ ለራሱ ያረጋገጣቸውን ወይም ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ያፀደቁለት በሆኑት ውብ ስሞችና ምሉዕ በሆኑት ባህርያቱ ማመን፤ አላህ እርሱን ከመግለፅ ያወገዛቸውንና ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለምም እርሱን ከመግለፅ ያወገዟቸውን ስምና ባሕርያት ውድቅ ማድረግ፤ የአላህ ስምና ባህሪያት በሙሉነት (ፍፁምነት) እና በውበት ጥግ የደረሱ ናቸው። {እርሱንም የሚመስለው ምንም ነገር የለም፤ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።}
ሁለተኛው ማዕዘን፦ በመላኢኮች ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿الْحَمْدُ لِلَّهِ فَاطِرِ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ جَاعِلِ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا أُولِي أَجْنِحَةٍ مَثْنَى وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ يَزِيدُ فِي الْخَلْقِ مَا يَشَاءُ إِنَّ اللَّهَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ﴾ "ምስጋና ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ፣ መላእክትን ባለ ሁለት ሁለት፣ ባለ ሶስት ሶስትም፣ ባለ አራት አራትም ክንፎች የኾኑ መልክተኞች አድራጊ ለኾነው አላህ ይገባው፡፡ በፍጥረቱ ውስጥ የሚሻውን ይጨምራል፡፡ አላህ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነውና።"(ፋጢር፡ 1)
መላእክት የማይታዩ ዓለም፤ ከብርሃን የተፈጠሩ የአላህ ባሪያዎች እንዲሁም ለእርሱ ታዛዥና ተገዢ ያደረጋቸው ባርያዎቹ መሆናቸውን እናምናለን።
ታላቅ የሆኑ ፍጥረት ናቸው፤ ስለ ብቃታቸውም ይሁን ስለቁጥራቸው የሚያውቀው የበላይ የሆነው አላህ ብቻ ነው። እያንዳንዳቸውም አላህ ለነርሱ ለይቶ የሰጣቸው መገለጫዎች፣ ስሞች እና ኃላፊነቶች አሏቸው፤ ከእነርሱም መካከል ጂብሪል ከአላህ ወደ መልዕክተኞች ወሕይ (ራዕይ) እንዲያወርድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ሦስተኛው ማዕዘን፦ በመጽሐፍቱ ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿قُولُوا آمَنَّا بِاللَّهِ وَمَا أُنْزِلَ إِلَيْنَا وَمَا أُنْزِلَ إِلَى إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ وَإِسْحَاقَ وَيَعْقُوبَ وَالْأَسْبَاطِ وَمَا أُوتِيَ مُوسَى وَعِيسَى وَمَا أُوتِيَ النَّبِيُّونَ مِنْ رَبِّهِمْ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْهُمْ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ﴾ «በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡[አል-በቀራህ: 136]
መለኮታዊ (ቅዱሳን) መጻሕፍት ሁሉ የአላህ ቃል መሆናቸው ጽኑ (ቁርጠኛ) እምነት ማሳደርና እውነት ብሎ መቀበል።
ከአላህ ዘንድ በመልእክተኞቹ ላይ የተወረደ ወደ ባሮቹ (የተላለፈ) ግልፅ የሆነ እውነት ነው።
አላህ መልዕክተኛውን ሙሐመድን የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ወደ ሰዎች ሁሉ በመላክ (ከእርሳቸው በፊት ለነበሩ ነብያት የተሰጡ) ቀደምት ህግጋትን ሁሉ ለእርሳቸው በሰጣቸው ህግ እንዲሻሩ አድርጓል፤ እና የተከበረውን ቁርኣንንም የሁሉም ሰማያዊ (መለኮታዊ) መጽሃፍት የበላይ (ተቆጣጣሪ) እና ሻሪ እንዲሆን አድርጎታል። እንዲሁም አላህ የተከበረውን ቁርኣን ከማንኛውም ዓይነት ለውጥ ወይም መዛባት ለመጠበቅ ሙሉ ኃላፊነቱንም ወስዷል።﴿إِنَّا نَحْنُ نَزَّلْنَا الذِّكْرَ وَإِنَّا لَهُ لَحَافِظُونَ﴾ "እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው፡፡ እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።"[አል-ሒጅር: 9]ምክንያቱም ቅዱስ ቁርኣን አላህ ለሰው ልጆች ያወረደው የመጨረሻው የእርሱ መጽሐፍ ነው፤ መልዕክተኛውም ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን የመጨረሻ መልዕክተኛ ናቸው፤ የእስልምና ሃይማኖትም አላህ እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ ለሰው ልጆች የወደደላቸውና የመረጠላቸው ሃይማኖት ነው።﴿إِنَّ الدِّينَ عِنْدَ اللَّهِ الْإِسْلَامُ﴾ "አላህ ዘንድ የተወደደው ሀይማኖት እስልምና ነው።"[አሊ-ዒምራን ፡19]
የበላይ የሆነው አላህ በመጽሐፉ (ቁርኣን) ውስጥ የጠቀሳቸው መለኮታዊ መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው፡-
የተከበረው ቁርኣን፡- አላህ በነብዩ ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ላይ ያወረደው።
ተውራት (ኦሪት)፡- አላህ በነቢዩ ሙሳ (ሙሴ) የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ላይ ያወረደው።
ኢንጂል (ወንጌል)፦ አላህ በነቢዩ ዒሳ (ኢየሱስ) የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ላይ ያወረደው።
ዘቡር (መዝሙረ ዳዊት)፦ አላህ በነቢዩ ዳዉድ (ዳዊት) የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ላይ ያወረደው።
ሱሑፍ ኢብራሂም፦ አላህ በነቢዩ ኢብራሂም (አብረሃም) የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን ላይ ያወረደው።
አራተኛው ማዕዘን፡ በመልዕክተኞች ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿وَلَقَدْ بَعَثْنَا فِي كُلِّ أُمَّةٍ رَّسُولاً أَنِ اعْبُدُواْ اللّهَ وَاجْتَنِبُواْ الطَّاغُوتَ﴾ "በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል፡፡"[አን-ነሕል፡ 36]
ኃያሉ አላህ በሁሉም ህዝቦች ውስጥ መልዕክተኞችን ብቸኛና ምንም ዓይነት አጋር የሌለውን አላህ በብቸኝነት እንዲገዙት እና ከእርሱም ውጪ በሚመለኩት ሁሉ እንዲክዱ ጥሪ እንዲያደርጉ እንደላካቸው ጽኑ (ቁርጠኛ) እምነት ማኖር ነው።
ሁሉም ነብያት ሰዎች፣ ወንዶች፣ የአላህ ባሮች፣ እውነተኞችና የታመኑ፣ አላህን ፈሪና ታማኝ፣ ወደ ቅን ጎዳና የተመሩና ሌሎችንም የሚመሩ፣ እውነተኝነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ተአምራትን አላህ የሰጣቸው እና አላህ የሰጣቸውን መልዕክት ሁሉ ያስተላለፉ ናቸው፤ ሁሉም ነብያት በግልፅ እውነት እና በትክክለኛ መመሪያ ላይ ነበሩ።
ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተላኩት ነብያት የዲን መሰረት (ሃይማኖታዊ መርህ) የሆነው ጥሪያቸው አንድ አይነት ነው፤ ይሀውም አላህን በአምልኮ ብቸኛ ማድረግና በእርሱ ላይ ከማጋራት መቆጠብ ነው።
አምስተኛው ማዕዘን፡ በመጨረሻው ቀን ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿اللَّهُ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ لَيَجْمَعَنَّكُمْ إِلَى يَوْمِ الْقِيَامَةِ لَا رَيْبَ فِيهِ وَمَنْ أَصْدَقُ مِنَ اللَّهِ حَدِيثًا﴾ "አላህ ከእርሱ በስተቀር አምላክ የለም፡፡ ወደ ትንሣኤ ቀን በርሱ ጥርጥር የሌለበት ሲኾን በእርግጥ ይሰበስባችኋል፡፡ በንግግርም ከአላህ ይበልጥ እውነተኛ ማነው?"(አንኒሳእ፡ 87)
ልዕለ ኃያል የሆነው ጌታችን በተከበረው መጽሐፉ (ቁርኣን) ወይም ነቢያችን ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን የነገሩንን የሰው ልጅ መሞት፣ ከሞተም በኋላ መቀስቀስ፣ ትንሣኤ፣ ምልጃ፣ ሚዛን፣ ምርመራ (ሒሳብ መደረግ)፣ ጀነት እና ጀሀነም እና ሌሎች ከመጨረሻው ቀን ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሁሉ በጽኑ ማመን ነው።
ስድስተኛው ማዕዘን፡ መልካምም ሆነ መጥፎ በአላህ ቀደር (ቅድመ ውሳኔ) ማመን
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿إِنَّا كُلَّ شَيْءٍ خَلَقْنَاهُ بِقَدَرٍ﴾ "እኛ ሁሉን ነገር በልክ ፈጠርነው፡፡"(አል ቀመር፡ 49)
በዚህ ዓለም ውስጥ በፍጥረታት ላይ የሚደርሰው ክስተት ሁሉ ጥራት ይገባውና የልዑሉ አላህ ዕውቀት እና ቀደር (ቅድመ ውሳኔ) መሆኑን፤ እነዚህ ቅድመ ውሳኔዎች የተጻፉትም የሰው ልጅ ከመፈጠሩ በፊት መሆኑን፤ የሰው ልጅ ነፃ ምርጫ እንዳለውና የድርጊቱ እውነተኛ ፈፃሚ ራሱ መሆኑንም እናምናለን። ይህ ሁሉ ታዲያ ከአላህ እውቀትና ፈቃድ ውጭ የሚሆን አይደለም።
በቀደር (ቅድመ ውሳኔ) ማመን አራት ደረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነው ፦
አንደኛ፦ ሁሉን የሚያካትትና ሙሉ በሆነው የአላህ ዕውቀት ማመን።
ሁለተኛ፦ እስከ ዕለተ ትንሳኤ ድረስ የሚሆነውን (የሚከሰተውን) ነገር ሁሉ አላህ እንደጻፈው ማመን።
ሦስተኛ፦ ተፈፃሚ በሆነው የአላህ ፈቃድ እና ሙሉ በሆነው ኃይሉ ማመን፤ አላህ የሚፈልገው ይሆናል የማይፈልገው ነገር ደግሞ አይሆንም።
አራተኛ፦ አላህ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው ብሎ ማመንና በመፍጠሩ ላይም ምንም ዓይነት አጋር እንደሌለው ማመን።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ﴾ "አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል፡፡"(አል በቀራህ፡ 22)የአላህ መልዕክተኛ ሰላትና ሰላም በእርሳቸዉ ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፦"እኔ ውዱእ በማደርግበት አኳኃን ውዱእ አድርጉ።"የሶላትን ትልቅ ደረጃ ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል አንዱ አላህ ከሶላት በፊት ጦሀራን (መፀዳዳት) መደንገጉ ነው፤ ለሶላቱ ትክክለኝነትና ተቀባይነትም መስፈርት አድርጎታል፤ ጦሃራ የሶላት ቁልፍ ነው (ለመፈፀም የመጀመሪያው እርምጃ ነው)፤ ከጥቅሙም መካከል ንቃተ ህሊና በመጨመር ልብ ሶላት ለመስገድ እንዲናፍቅ ያደርጋል።የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፦"ንፅህና የእምነት ግማሽ ነው ... ሶላት ደግሞ ብርሃን ነው።"የአላህ መልዕክተኛ ሰላትና ሰላም በእርሳቸዉ ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፦" ዉዱእ አሳምሮ በአግባቡ ያደረገ፤ ኃጢአቱ ከአካሉ ይወጣል (ይራገፍለታል)።"
አንድ የአላህ ባሪያ በዉዱእ አካላዊ ንጽህናውን የሚጠብቅ ሲሆን፤ ይህን የአምልኮ ተግባር በኢኽላስ (ሥራውን ለአላህ ብቻ ጥርት በማድረግ) እና የነቢዩን የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን መመሪያ በመከተል ውስጣዊ ንፅህናውን ይጠብቃል።
ውዱእ ማድረግ ግዴታ የሚያስፈልጋቸው የአምልኮ ተግባራት፦
ግዴታም ሆነ ግዴታ ያልሆኑ (ሱና) ሶላት።
በካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ለማድረግ።
ሙስሐፍ (ቁርአን) መንካት።
ዉዱእም ሆነ የገላ ትጥበት የማከናውነው ጣሃራ (ንፁህ) በሆነ ውኃ ነው።
ንፁህ ውኃ የሚባለው፦ ከሰማይ የወረደ ወይም ከምድር የፈለቀ ውኃ ሁሉ ሲሆን ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይቀይር የቆየ ከሆነና የውሃ ንፅህናን ከሚያሳጡ ሦስቱ ባህሪያት የቀለም፣ የጣዕም ወይም የሽታ መለወጥ ያላጋጠመው ከሆነ ነው።
የዉዱእ አደራረግ እማራለሁ
በመጀመርያ ደረጃ፡ ኒያህ ማድረግ (በልብ ማሰብ) ፤ ኒያህ ማለት ወደ አላህ ለመቃረብ አምልኮን ለመፈፀም በልብ ውስጥ ያለን ቁርጠኝነት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ፡ ሁለት መዳፎችን መታጠብ።
በሶስተኛ ደረጃ፡ መጉመጥመጥ (መድመዳህ)።
መድመዷህ ማለት፦ ውኃ አፍ ውስጥ አስገብቶ ተጉመጥምጦ መትፋት ነው።
በአራተኛ ደረጃ፡ መሰርነቅ (ኢስቲንሻቅ)።
መሰርነቅ ማለት፦ ወደ ውስጥ አፍንጫ ውኃን በደንብ መሳብ ነው።
ኢስቲንሣር ማለት፦ በአፍንጫ ውስጥ ያሉ እንደ ንፍጥ እና መሰል ነገራቶችን ማስወጣት ነው።
በአምስተኛ ደረጃ፡ ፊትን ማጠብ።
የፊት ድንበሩ፡-
ፊት ማለት: የሚቅጣጩበት የሰውነት ክፍል ነው።
የጎን ስፋቱ: ከአንዱ ጆሮ እስከ ሌላኛው ጆሮ ድረስ ሲሆን
የፊት ወሰን ርዝመቱ ደግሞ፡ በተለምዶ ፀጉር ከሚጀምርበት የግንባር ክፍል እስከ የአገጫችን መጨረሻ ድረስ ነው።
ፊቱን ማጠብ በላዩ ላይ ያሉትን ነገሮች ማለትም እንደ ለስላሳ ፀጉር እንዲሁም በጆሮው ፊት ለፊት ላይ የበቀለ ፀጉር እና ውጫዊው የጆሮ ለስላሳ ሥጋ ጋር ያለውን ፀጉር ማጠብን ያጠቃልላል።
አልበያድ ማለት፦ በጆሮው ፊት ለፊት ላይ የበቀለ ፀጉር ነው።
አልዒዛር ማለት ደግሞ፦ ከጭንቅላቱ ውስጠኛው ክፍል ጋር ከመጨረሻው የጆሮ ቀዳዳ ትይዩ በአጥንት ላይ ያለው ፀጉር ነው።
ሌላኛው ፊትን ከማጠብ የሚካተተው ሁሉንም ጎልተው የሚታዩትን የፂም ፀጉር እና ከእርሱ ዘልቆ ከውስጥ ያለውንም ማጠብ ነው።
በስድስተኛ ደረጃ፡ ከጣት ጫፎች ጀምሮ እስከ ክርኖች ድረስ እጆችን መታጠብ።
ክርኖችን ማጠብ እጆችን ከመተጠብ ግዴታ ውስጥ ይካተታል።
በሰባተኛ ደረጃ፡ በተነከሩ እጆች ጭንቅላትን እና ጆሮን አንድ ጊዜ ማበስ።
ይሀውም ከፀጉር መብቀያው ግንባር ይጀምርና ወደ ጭንቅላቱ ጀርባ ማጅራቱ ድረስ ይወስዳቸውና ከዚያም እንደገና ወደጀመረበት በመመለስ ነው።
ጠቋሚ ጣቶቹን ወደ ጆሮው ያስገባል።
አውራ ጣቱን ከጆሮው ጀርባ በማሳለፍ (በማሻገር) የጆሮውን ፊት እና ኋላ ያብሳል።
በስምንተኛ ደረጃ፡ እግሮቹን ከእግር ጣቶች መጀመሪያ አንስቶ እስከ ቁርጭምጭሚት ድረስ ማጠብ፤ ቁርጭምጭሚቶቹን ማጠብ ግዴታ መታጠብ ካለበት የእግሮቹ ክፍሎች ውስጥ ይካተታል።
ቁርጭምጭሚቶች የሚባሉት፡- በእግር ባት ስር ወጣ ብለው የሚታዩት አጥንቶች ናቸው።
ዉዱእን የሚያበላሹ ነገሮች፡-
1 እንደ ውኃ ሽንት፣ ሰገራ፣ ፈስ፣ መንይ እና መዝይ መሰል በውኃ ሽንት እና አይነ ምድር መውጫ ቦታዎች በኩል የሚወጡ ነገሮች፡፡
2. ጭልጥ ባለ እንቅልፍ ወይም ራስን በመሳት ወይም በስካር ወይም በእብደት ምክንያት የአዕምሮ መሸፈን
3. የገላ ትጥበትን ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ፤ ለምሳሌ ጀናባ መሆን፣ የወር አበባ እና የወሊድ ደም መፍሰስ።
አንድ ሰው (ከሽንት ወይም ከሰገራ) ተፀዳድቶ ከጨረሰ በኃላ ቢቻል ንፁህ በሆነ ውኃ ይህ በላጩ ነው ካልቻለ ደግሞ ከውኃ ውጪ ባሉ ነጃሳውን ማፅዳት የሚችሉ ንፁህ ሌሎች ነገሮች ለምሳሌ ድንጋይ፣ ወረቀት (ሶፍት) በመሳሰሉት ነጃሳውን ማስወገድ ግዴታ ነው። (በውኋ ምትክ የምንጠቀማቸው ነገሮች) ንፁህና በሚፈቀድ ነገር የተሰሩ ከመሆነቸውም ባሻገር ብዛታቸውም ሶስት ጊዜ ማጽዳት የሚያስችሉ ወይም ከዚያ በላይ መሆን ይገባቸዋል።
ኹፍ ወይም ካልሲዎችን በሚለብሱበት ጊዜ በሚከተሉት ቅድ ሁኔታዎች ውስጥ መሰረት እግሮችን መታጠብ ሳያስፈልግ በእነሱ ላይ ማበስ ይቻላል። ቅድመ ሁኔታዎቹም የሚከተሉት ናቸው፦
1. ኹፎቹ የተለበሱት/የተደረጉት ከትንሹ ሐደሥም ይሁን ከትልቁ ሐደሥ ሙሉ በሙሉ ጠሀራ ከሆነ በኋላ መሆን አለበት።
2. ካልሲዎቹ ወይም ኹፎቹ ጡሀራ መሆን አለባቸው፤ ነጃሳ መሆን የለባቸውም።
3. የታበሱት (ለማበስ) በተፈቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆን አለበት።
4. በህጋዊ (ሐላል) በሆነ መልኩ የተገኙ መሆን አለባቸው፤ ለምሳሌ የተሰረቁ ወይም የተዘረፉ መሆን የለባቸውም።
"ኹፍ" የሚባሉት፦ ከቀጭን ቆዳ የተሠሩ የእግር ጫማዎችና የመሳሰሉት ናቸው፤ ተረከዝን የሚሸፍኑ እስከሆኑ ድረስ ጫማዎችም ብይናቸው ተመሳሳይ ነው።
ካልሲ የሚባሉት፡- አንድ ሰው በእግሩ ላይ የሚለብሰው ከጥጥና ከመሳሰሉት የሚሠራ ነው፤ (የእግር ሹራብ) በመባል ይታወቃል።
በኹፍ ላይ ማበስ የመደንገግ ጥበቡ፦
በኹፍ ላይ ማበስ የተፈቀደበት ጥበብ ኹፋቸውን ወይም ካልሲያቸውን አውልቀው እግራቸውን ለማጠብ ለሚከብዳቸው ሙስሊሞች በተለይም በክረምት እና በከባድ ብርድ እንዲሁም በሚጓዙበት ወቅት ለማግራት እና ቀለል ለማድረግ ነው።
የማበሻ ጊዜ ገደብ
ለነዋሪ፦ አንድ ቀን ከነሌሊቱ (24 ሰዓት)።
ለመንገደኛ፦ ሦስት ቀናት ከነለሊታቸው። (72 ሰዓት)
የማበሻ ጊዜ ስሌት የሚጀምረው ዉድእ ካጠፋ በኋላ በኹፍ ወይም በካልሲ ላይ ካበሰበት ጊዜ ጀምሮ ነው።
በኹፍ ወይም ካልሲ ላይ የሚታበስበት ስርዓት፦
1 እጆችዎን እርጥብ ያድርጉ።
2. ያረጠቡትን እጅዎን በእግሮ ላይኛው ክፍል ላይ (ከጣቶቾ ጫፍ እስከ እግሮ ጫፍ ድረስ) ያሳልፉ።
3. የቀኝ እግር በቀኝ እጅ፤ የግራ እግርን በግራ እጅዎ ያብሱ።
ማበስን የሚያበላሹ ነገሮች፦
1. ገላ ትጥበትን መታጠብ ግዴታ የሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ።
2. የማበሻ ጊዜ ገደብ መጠናቀቅ።
የትኛውም ወንድም ይሁን ሴት የግብረ ስጋ ግንኙነት ከፈፀሙ፤ ወይም አንቀላፍተውም ይሁን ነቅተው ሳሉ በስሜት የዘር ፈሳሽ ከፈሰሳቸው የዚህኔ ሶላትን ለመስገድ ወይም ጦሃራ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለመፈፀም ትጥበት ግዴታ ይሆንባቸዋል። እንደዚሁም አንዲት ሴት ከወር አበባ እና ከወሊድ ደም ከጠራች በኋላ ሶላት ከመስገዷ ወይም ጦሃራ የሚያስፈልጋቸውን ተግባራት ከመፈፀሟ በፊት ትጥበት ግዴታ ይሆንባታል።
የትጥበት ስርዓት እንደሚከተለው ነው፦
ሙስሊሙ በማንኛውም አኳኃን መላ ሰውነቱን በውሃ ማዳረስ አለበት፤ ከእነዚህም ውስጥ መጉመጥመጥና መሰርነቅ (ውኃ በአፍንጫ አስገብቶ ማስወጣት) ይገኝበታል። ሰውነቱን ሙሉ በውሃ ካዳረሰ ትልቁ ሐደስ (ነጃሳ) ይወገዳል፤ ትጥበቱም የተሟላ ይሆናል።
ጀናባ የሆነ (ትጥበት ግዴታ የሆነበት) ሰው ገላውን እስኪታጠብ ድረስ የሚከተሉትን ማድረጉ የተከለከለ ነው፦
01 ሶላት መስገድ።
02 በካዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ማድረግ (መዞር)።
03 በመስጂድ ውስጥ መቆየት፤ ቆይታ ሳያደርግ ለማለፍ ብቻ ከሆነ ይፈቀዳል።
04 ቁርኣንን መንካት።
05 ቁርኣንን መቅራት።
አንድ ሙስሊም ራሱን የሚያጠራበት ውኃ ማግኘት ካልቻለ ወይም በህመም እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ውኃ መጠቀም ካልቻለና የሶላት ጊዜ እንዳያመልጠዉ ስጋት ካደረበት በአፈር ተያሙም ያደርጋል።
የአደራረግ ሁኔታውም በመጀመሪያ በሁለቱ እጆቹ (አፈሩን) አንድ ጊዜ ይመታዋል፤ ከዚያም ፊቱን እና እጆቹን ብቻ ያብሳል፤ የአፈሩ ጡሀራ መሆን ሊዘነጋ የማይገባው መስፈርት ነው።
ተየሙም በእነዚህ ነገሮች ይበላሻል፡-
1- ዉዱእ በሚያበላሽ ነገር ሁሉ ተየሙምንም ያበላሻል።
2- ተይሙም የተደረገለት ዒባዳ ከመጀመሩ በፊት ውሃ ከተገኘ።
አላህ በሙስሊሞች ላይ በቀን እና በሌሊት የሚሰገዱ አምስት ሶላቶችን ደንግጓል፤ እነርሱም፡- ፈጅር (ሌሊት የሚሰገደው)፣ ዙሁር (ቀትር የሚሰገደው)፣ አስር (ከሰዓት የሚሰገደው)፣ መግሪብ (በጀምበር መጥለቂያ ሰአት የሚሰገደው) እና ዒሻእ (ምሽት የሚሰገደው) ሶላት ናቸው።
ራሴን ለሶላት አዘጋጃለሁ
የሶላት ወቅት ሲገባ አንድ ሙስሊም ከትንሹ ሐደሥም ሆነ ተከስቶ ከሆነ ከትልቁ ሐደሥም ራሱን ያጸዳል።
ትልቁ ሐደሥ ማለት፦ መላ ሰውነትን መታጠብ የሚያስፈርድ ነው (ለምሳሌ ግብረስጋ ግንኙነት መፈፀም)።
ትንሽ ሐደሥ ማለት ደግሞ፦ ዉዱእ ማድረግ ግዴታ የሚያደርግ ነው።
አንድ ሙስሊም ሶላቱን መስገድ የሚገባው ከነጃሳ በጠራ ንፁህ ልብስ እና ንፁህ ሥፍራ እንዲሁም ሀፍረተ ገላውንም (ሶላት ውስጥ መሸፈን ያለበትን የአካል ክፍል) በአግባቡ ሸፍኖ ነው።
አንድ ሙስሊም በሶላት ጊዜ ገላውን በአግባቡ ሊሸፍንበት ተገቢ በሆነ ልብስ ማጌጥ አለበት። አንድ ወንድ በሶላት ወቅት በእምብርት እና ጉልበቱ መካከል ያለውን የአካሉ ክፍል ሳይሸፍን መስገድ አይፈቀድለትም።
ሴት ከሆነች ደግሞ ከፊቷና ከመዳፎቿ በስተቀር ሁሉንም የሰውነቷን ክፍሎች በሶላት ወቅት መሸፈን አለባት።
አንድ ሙስሊም ሶላት በሚሰግድበት ወቅት ለሶላት አስፈላጊ (የሶላቱ አካል) የሆኑትን ንግግሮችን ብቻ ይናገር፤ ኢማሙን (የሕብረት ሶላት የሚመራውን ሰው) በጥሞና ያዳምጥ፤ ሶላት ውስጥ ሆኖ ወደ ግራና ቀኝም አይዟዟር፣ ሶላት ውስጥ የሚባሉትንም ቃላት መሸምደድ ካልቻለ ሶላቱ እስኪያልቅ ድረስ ሱብሓነሏህ እና መሰል ዚክሮችን እያለ አላህን ያውሳ፤ ያወድሰውም፤ ይሁን እንጅ ሶላትን እና በውስጡ የሚባሉ ቃላቶችን ለመማር መቻኮል ይጠበቅበታል።
የሶላት አሰጋገድ ስርአትን እማራለሁ
በመጀመርያ ደረጃ፡ ልሰግደው ያሰብኩትን ሶላት እነይታለሁ፤ በልቦናየ አስበዋለሁ።
ውዱእ ካደረግኩም በኋላ ወደ ቂብላ (መካ ወደሚገኘው ካዕባህ) አቅጣጫ እቅጣጫለሁ፤ ከቻልኩኝ ቆሜ እሰግዳለሁ።
በሁለተኛ ደረጃ፡ እጆቼን በትከሻዎቼ ትይዩ አንስቼ ወደ ሶላት ውስጥ ለመግባት በማሰብ "አላሁ አክበር" እላለሁ።
በሶስተኛ ደረጃ: ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የተዘገበውን የመክፈቻ ዱዓ (ዱዓኡል ኢስቲፍታሕ) እላለሁ። ከመክፈቻ ዱዓዎች መካከል አንዱ የሚከተለው ነው፦(ሱብሓነከ አልላሁመ ወቢሐምዲከ፤ ወተባረከ ኢስሙከ፤ ወተዓላ ጀዱከ፤ ወላኢላሃ ገይሩከ) ((ትርጉሙም: አላህ ሆይ! ክብርና ምስጋና ላንተ ይሁን፤ ስምህ የተባረከ ነው፤ ልዕልናህም የተከበረ ነው፤ ካንተ በቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም።))በአራተኛ ደረጃ: የተረገመ ከሆነው ሰይጣን በአላህ ለመጠበቅ እንዲህ እላለሁ፦(አዑዙ ቢላሂ ሚነ አሽሸይጧን አርረጂም) ((ትርጉሙም: ከተረገመው ሰይጣን በአላህ እጠበቃለሁ))በአምስተኛ ደረጃ: ሱረቱል ፋቲሓን (አልሓምዱን) በየረከዓው (የሶላት እያንዳንዱ ክፍል) እቀራለሁ።﴿بسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَنِ الرَّحِيمِ (1) «ቢስሚልላሂ‐ር‐ሯሕማኒ‐ር‐ሯሒም» [ትርጉሙም: በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው] (1)الْحَمْدُ لِلَّهِ رَبِّ الْعَالَمِينَ (2) «አልሓምዱ ሊልላሂ ረቢል ዓለሚን» (ትርጉሙም: ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የተገባው ነው) (2)الرَّحْمَنِ الرَّحِيمِ (3) «አር‐ሯሕማኒ‐ር‐ሯሒም» (ትርጉሙም: እጅግ በጣም አዛኝ አዛኝ እጅግ በጣም ሩኅሩህ) (3)مَالِكِ يَوْمِ الدِّينِ (4) «ማሊኪ የውሚ‐ድ‐ዲን» (ትርጉሙም: የፍርዱ ቀን ባለቤት) (4)إِيَّاكَ نَعْبُدُ وَإِيَّاكَ نَسْتَعِينُ (5) «ኢይያከ ነዕቡዱ ወኢይያከ ነሰተዒን» (አንተን ብቻ እንገዛለን አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምንሃለን) (5)اهْدِنَا الصِّرَاطَ الْمُسْتَقِيمَ (6) «ኢህዲና‐ስ‐ሲሯጦል ሙስተቂም» (ትርጉሙም: ቀጥተኛውን መንገድ ምራን) (6)صِرَاطَ الَّذِينَ أَنْعَمْتَ عَلَيْهِمْ غَيْرِ الْمَغْضُوبِ عَلَيْهِمْ وَلَا الضَّالِّينَ(7)﴾. «ሲሯጦ‐ል‐ለዚነ አንዓምተ ዓለይሂም ቐይሪል መቕዱቢ ዓለይሂም ወለድዷሊን» (ትርጉሙም: የእነዚያ ፀጋህን የዋልክላቸውን ሰዎች መንገድ በነዚያ የተቆጣህባቸውን እና የተሳሳቱትንም አይደሉም።) (7)
ከሱረቱል ፋቲሓ በኋላ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ረከዓ ብቻ ሌሎች (ከአልፋቲሃ ውጪ) ያሉ የቁርዓን አንቀጾችን አነባለሁ። ሌሎች የቁርኣን አንቀጾችን ማንበብ ግዴታ አይደለም ነገር ግን ማድረጉ ትልቅ ምንዳ ያስገኛል።
በስድስተኛ ደረጃ: "አላሁ አክበር" ብዬ ከዚያም ጀርባዬ ቀጥ ብሎ በሚስተካከልበት ልክ በማጎንበስ፣ እጆቼ በጉልበቶቼ ላይ ጣቶቼን ከፈትፈት አድርጌ ሩኩዕ አደርጌ ሳለሁ "ሱብሓነ ረቢየ-አል-ዐዚም" እላለሁ። (ትርጉሙም: ታላቁ ጌታዬ ጥራት ተገባው)
በሰባተኛ ደረጃ: "ሰሚዐ'ሏሁ ሊማን ሐሚደህ" እያልኩ ከሩኩዕ ቀና እላለሁ። (ትርጉሙም: አላህ የአመስጋኙን ምስጋና ሰማ) እላለሁ። እጆቼንም በትከሻዎቼ ትይዩ ከፍ እያደረግኩኝ እነሳና ቀጥ ብዬ ስቆም፡- "ረብበና ወለከል ሐምድ" እላለሁ። (ትርጉሙም: ጌታችን ሆይ! ምስጋና ላንተ ነው።)
በስምንተኛ ደረጃ: "አላሁ አክበር" እያልኩ በእጆቼ፣ በጉልበቴ፣ በእግሬ ጣቶች፣ በግንባሬና በአፍንጫዬ መስገጃየ ላይ ተደፍቸ ሱጁድ አደርጋለሁ። ከዚያም ሱጁድ ላይ (በግንባሬ ተደፍቼ) እያለሁም እንዲህ እላለሁ፡- "ሱብሐነ ረብቢየል-አዕላ" እላለሁ። (ትርጉሙም: ከሁሉ የበላይ የሆነው ጌታዬ ጥራት ተገባው)
በዘጠነኛ ደረጃ: "አላሁ አክበር" እያልኩ ከሱጁድ (ስግደት) ቀና ብየ ጀርባዬን ቀጥ አድርጌ በግራ እግሬ ውስጠኛው ክፍል ተቀምጬ የቀኝ እግሬን ተረከዝ ደግሞ ቀጥ አድርጌ እተክለዋለሁ። ከዚያም፡- "ረብቢ ኢግፊር ሊ" እላለሁ።(ትርጉሙም: ጌታዬ ሆይ! ኃጢአቴን ማረኝ)
በአስረኛ ደረጃ: (አላሁ አክበር) እያልኩ እንደገና ልክ እንደ መጀመሪያው ሱጁድ አደርጋለሁ።
በአስራ አንደኛ ደረጃ: "አላሁ አክበር" እያልኩ ተስተካክየ ከሱጁድ እነሳለሁ፤ ከዚያም ይህንን በመጀመርያዋ ረከዓ ያደረግኩትን ስርአት ሁሉ በቀሪዎቹ የሶላት ክፍሎችም ላይ እፈጽመዋለሁ።
ከዙህር፣ ዐስር፣ መግሪብ እና ዒሻእ ሶላት ሁለተኛ ረከዓ በኋላ የመጀመሪያውን ተሸሁድ (አተሕያቱ) ለማለት እቀመጣለሁ። ይሀውም፦"አት‐ተሒያቱ ሊላሂ ወስ‐ሶላዋቱ ወጥ‐ጠይ‐ዪባቱ፣ አስ‐ሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካትሁ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፡፡" "ትርጉሙም: ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን፤ ከአላህ ሌላ በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባርያና መልዕክተኛው መሆናቸውንም እመሰክራለሁ፡፡"ከዚያም ለሦስተኛው ረከዓህ እቆማለሁ።በእያንዳንዱ ሶላት የመጨረሻ ረከዓ ላይ የመጨረሻውን ተሸሁድ ለማለት እቀመጣለሁ። ይሀውም፦"አትተሒያቱ ሊላሂ ወስሶላዋቱ ወጥጠይዪባቱ ፣ አስሰላሙ ዐለይከ አይዩሀን-ነቢይዩ ወረሕመቱልላሂ ወበረካትሁ ፤ አስሰላሙ ዐለይና ወዓላ ዒባዲላሂ አስሷሊሒነ ፣ አሽሀዱ አንላኢላሀ ኢልለልላህ ወአሽሀዱ አንነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉሁ፡፡ አልላሁምመ ሰልሊ ዐላ ሙሐመዲን ወዐላ ኣሊ ሙሐመዲን ከማ ሶልለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡ አልላሁምመ ባሪክ ዓላ ሙሐመዲን ወዐላ አሊ ሙሐመዲን ከማ ባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ወዓላ አሊ ኢብራሂመ ኢንነከ ሐሚዱን መጂድ።" "ትርጉሙም: ክብርና ልዕልና እንዲሁም ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ ለአላህ ናቸው። አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣ እዝነቱና በረከቶች በእርሶ ላይ ይስፈን፤ ሰላም በእኛና በአላህ ደጋግ ባሮችም ላይ ይስፈን። ከአላህ በቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ አገልጋይና መልዕክተኛ መሆናቸውን እመሰክራለሁ፤ አላህ ሆይ! ውዳሴህን ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸው አውርድላቸው፤ አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና። አላህ ሆይ! ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው ረድዔትን እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸውም ረድዔትን አውርድላቸው። አንተ ምስጉንና ኋያል (የላቅክ) ነህና።"
በአስራ ሁለተኛ ደረጃ: ያንን ሁሉ ካደረግኩ በኋላ ሶላቴን ለማጠናቀቅ በማሰብ ጭንቅላቴን ወደ ቀኝ እያዞርኩኝ "አስሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ" (ትርጉሙም: የአላህ ሰላምና እዝነት በናንተ ላይ ይሁን) ከዚያም ጭንቅላቴን ወደ ግራም እያዞርኩኝ "አስሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱላህ" እላለሁ። ይህንን ባደረግኩ ጊዜ የሶላት ተግባሬን ፈጸምኩ ማለት ነው።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُلْ لِأَزْوَاجِكَ وَبَنَاتِكَ وَنِسَاءِ الْمُؤْمِنِينَ يُدْنِينَ عَلَيْهِنَّ مِنْ جَلَابِيبِهِنَّ ذَلِكَ أَدْنَى أَنْ يُعْرَفْنَ فَلَا يُؤْذَيْنَ وَكَانَ اللَّهُ غَفُورًا رَحِيمًا﴾ "አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶቸህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው፡፡ ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡"(አል አህዛብ ፡ 59)አላህ ሙስሊም ሴት ላይ ሒጃብ መልበስ፣ "ዓውራ"ዋን ብሎም መላ የአካል ክፍሏን ለእርሷ ባዕድ ከሆኑ ወንዶች በሀገሯ (በአካባቢዋ) በተለመዱ ልብሶች እንድትሸፍን ግዴታ አድርጎባታል። ባሏ እና ከዝምድናዋ አንፃር ለጋብቻ የማይፈቀዱላት (መሕረሟ) ዘንድ ካልሆነ ሒጃቧን ማውለቅ አይፈቀድላትም። "መሕረም" ማለት፦ አንዲት ሙስሊም ሴት ከዝምድና አንፃር ማግባት ፍፁም የማይፈቀድላቸው ናቸው፤ እነርሱም፦(አባት ከፍ ያለ ቢሄድም (አያት፣ ቅድመ አያት ወዘተ)፣ ልጅ ዝቅ እያለ ቢወርድም (የልጅ ልጅ፣ የልጅ ልጅ ልጅ ወዘተ)፣ በአባት በኩል አጎቶች፣ በእናት በኩል አጎቶች፣ ወንድም፣ የወንድም ልጅ፣ የእህት ልጅ፣ የእናት ባል (የእንጀራ አባት )፣ የባል አባት ከፍ እያለ ቢሄድም፣ የባል ልጅ ዝቅ እያለ ቢወርድም፣ የጥቢ (የጡት) ወንድም፣ የጥቢ (የጡት) እናት ባል እርሷን ሊያገቧት አይፈቀድላቸውም። በስጋ ዝምድና ምክንያት የሚከለከል ነገር ሁሉ በጥቢ ምክንያትም የተከለከለ ይሆናል)።
ሴት ልጅ ሒጃቧን ስትለብስ መጠበቅ ያለባት መስፈርቶች፦
የመጀመሪያ: ሙሉ የአካል ክፍልን የሚሸፍን መሆን አለበት።
ሁለተኛ: አንዲት ሴት ራሷን ለማስጌጥ ብላ የምትለብሰው ልብስ መሆን የለበትም።
ሦስተኛ: የውስጥ አካሏን (ገላዋን) የሚያሳይ መሆን የለበትም።
አራተኛ፡ ሰፊና ለቀቅ ያለ እንጅ የተጣበቀ ሆኖ የሰውነቱን ቅርጿን የሚያሳይ መሆን የለበትም።
አምስተኛ፡ ሽቶ የተቀባ (መአዛ ያለው) መሆን የለበትም።
ስድስተኛ፡- ከወንዶች ልብስ ጋር የተመሳሰለ መሆን የለበትም።
ሰባተኛ፡- ሙስሊም ያልሆኑ ሴቶች በአምልኳቸውም ሆነ በበዓላቶቻቸው የሚለብሱት ልብስ ጋር የተመሳሰለ መሆን የለበትም።
ከሙእሚን (አማኝ) ባህሪያት መካከል፦
የላቀው አላህ እንዲህ ኣለ፡﴿إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ الَّذِينَ إِذَا ذُكِرَ اللَّهُ وَجِلَتْ قُلُوبُهُمْ وَإِذَا تُلِيَتْ عَلَيْهِمْ آيَاتُهُ زَادَتْهُمْ إِيمَانًا وَعَلَى رَبِّهِمْ يَتَوَكَّلُونَ﴾ "ፍጹም ምእምናን እነዚያ አላህ በተወሳ ጊዜ ልቦቻቸው የሚፈሩት፣ በነሱም ላይ አንቀጾቻችን በተነበቡ ጊዜ እምነትን የሚጨምሩላቸው፣ በጌታቸውም ላይ ብቻ የሚመኩት ናቸው፡፡"(አል አንፋል፡ 2)
በንግግሩ እውነተኛ ነው አይዋሽም፤
ቃል ኪዳኑንም ይሞላል፤ ቃሉንም ይፈጽማል፤
በክርክርም ጊዜ ድንበር አያልፍም፤
አማና (አደራን) ይወጣል፤
ለራሱ የሚወደውን ለሙስሊም ወንድሙም ይወዳል፤
ቸር ነው፤
ለሰዎችም መልካም (በጎ) ይውላል፤
ዝምድናንም ይቀጥላል፤
የአላህንም ቀደር (ቅድመ ውሳኔ) ወዶ ይቀበላል፤ በምቾት ጊዜ አላህን ያመሰግናል በችግር ጊዜ ደግሞ ይታገሳል።
ሐያእ (ሀፍረትን) የተላበሰ ነው፤
ለፍጥረታት አዛኝ ነው፤
ልቡ ከምቀኝነት የፀዳ፤ አካሉ ደግሞ በሌሎች ላይ ድንበር ከማለፍ ንፁህ ነው።
ለሰዎችም ይቅር ባይ ነው፤
አራጣ አይበላም በእርሱም አይሠራም፤
ዝሙትን አይፈጽምም፤
አስካሪ መጠጥ አይጠጣም፤
ለጎረቤቶቹም መልካምን ይውላል፤
አይጨቁንም አያታልልም፤
አይሰርቅም አይተናኮልም፤
ወላጆቹ ሙስሊም ባይሆኑም እንኳን በጎ ይውልላቸዋል፤ በመልካም ነገርም ይታዘዛቸዋል፤
ልጆቹን በመልካም አስተዳደግ ይንከባከባቸዋል፣ ሸሪዓዊ ግዴታቸውንም እንዲወጡ ያዛቸዋል፣ ከመጥፎ እና እርባነ ቢስ ከሆኑ ነገሮችም ይከለክላቸዋል።
ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች በሃይማኖታዊ ስርዓታቸውም ይሁን የእነርሱ መለያና መገለጫ በሆኑ ድርጊቶቻቸው እነርሱን አይመስልም።
ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦﴿مَنْ عَمِلَ صَالِحًا مِنْ ذَكَرٍ أَوْ أُنْثَى وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَلَنُحْيِيَنَّهُ حَيَاةً طَيِّبَةً وَلَنَجْزِيَنَّهُمْ أَجْرَهُمْ بِأَحْسَنِ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ﴾ "ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ኾኖ በጎን የሰራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፡፡ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን፡፡"[አን-ነሕል 97]በሙስሊም ልብ ውስጥ ደስታን እና ምቾትን ከሚፈጥሩ ታላላቅ ነገሮች አንዱ የማንም ህያውም ይሁን ሙት ወይም ጣዖታት ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልገው ከጌታው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መፍጠሩ ነው። ከፍ ያለው አላህ በተከበረ ቁርኣኑ ላይ ሁል ጊዜ ለባሮቹ ቅርብ እንደሆነ፣ ዱዓቸውንም እንደሚሰማቸውና ምላሽም እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡-﴿وَإِذَا سَأَلَكَ عِبَادِي عَنِّي فَإِنِّي قَرِيبٌ أُجِيبُ دَعْوَةَ الدَّاعِ إِذَا دَعَانِ فَلْيَسْتَجِيبُوا لِي وَلْيُؤْمِنُوا بِي لَعَلَّهُمْ يَرْشُدُونَ﴾ "ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡ ስለዚህ ለኔ ይታዘዙ፤ በኔም ይመኑ፤ እነሱ ሊመሩ ይከጀላልና፡፡"(አልበቀራህ፡186)ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ እንድንለምነው (ዱዓእ እንድናደርግ) አዞናል፤ ይህንንም ጉዳይ (ዱዓእን) አንድ ሙስሊም ወደ ጌታው ከሚቃረብበት ታላላቅ ዒባዳዎች (አምልኮዎች) መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል። አላህ እንዲህ ብሏል፡-﴿وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ﴾ "ጌታችሁም አለ፤ ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ "(ጋፊር፡60)መልካም የሆነ እውነተኛ ሙስሊም ዘወትር ጌታውን ከጃይ ነው። ሁልጊዜም አላህን መለመን እና በመልካም ስራም ወደ እርሱ መቃረብ ይጠበቅበታል።
አላህ በዚህ ከውን (ፍጥረተ ዓለም) ውስጥ ያስገኘን ለታላቅ ጥበብ እንጂ በከንቱ አልፈጠረንም፤ ይሀውም የተፈጠርንበት ጥበብ እርሱን ብቻ በብቸኝነት እንድናመልክና በእርሱ ላይ ምንንም እንዳናጋራ ነው። ማህበራዊም ሆነ ግላዊ የሕይወት ጉዳያችንን ስርዓት የሚያስተካክል የተሟላ መለኮታዊ ሃይማኖት ደንግጎልናል። በዚህም ፍትሃዊ የሆነ የሸሪዓ ህግ አምስቱን የህይወት አስፈላጊ መሰረቶችን ማለትም ሃይማኖታችን፣ ሕይወታችን፣ ክብራችን፣ አዕምሮአችን እና ንብረታችን ጠብቆልናል። በመሆኑም የሸሪዓን መመርያን በመከተል ክልከላዎቹንም (እርም የተደረጉትን) በመራቅ ህይወቱን የኖረ ሰው በርግጥም እነዚህን አስፈላጊ መሰረቶችን ተጠብቆለት አስደሳችና የተፈጋጋ ህይወትን ይኖራል።
ሙስሊሙ ከጌታው ጋር ያለው ቁርኝት (ትስስር) እጅግ ጥልቅ በመሆኑ ለነፍሱ መረጋጋትና ዘና ማለትን ይፈጥራል፤ ደህንነት እና ደስታንም ይጎናፀፋል፤ አላህ ከእርሱ ጋ እንደሆነ እና እንክብካቤውና ጥበቃው ከእርሱ የማይለየው እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል። አላህ እንዲህ ብሏል፡-﴿اللَّهُ وَلِيُّ الَّذِينَ آمَنُوا يُخْرِجُهُمْ مِنَ الظُّلُمَاتِ إِلَى النُّورِ﴾ "አላህ የእነዚያ ያመኑት ሰዎች ረዳት ነው፡፡ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል፡፡ "[አል-በቀራህ: 257]
ይህ ታላቅ ግንኙነት ሙስሊሙን እጅግ በጣም አዛኝ የሆነውን አላህን በማምለክ የደስታ ስሜት እንዲሰማው እና እርሱን ለመገናኘት እንዲመኝ የሚያደርግ መንፈሳዊ ሁኔታ ነው። የእምነትን (የኢማን) ጥፍጣና ሲያጣጥም ልብን በደስታ ይሞላል።
ይህን የኢማን ጥፍጥና መልካም ሥራን በመስራትና ከመጥፎ ነገር በመራቅ ከቀመሰው በቀር ደስታውን ሊገለጽ አይችልም። ለዚህም ሲሉ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፡-(አላህን ጌታው፣ እስልምናን እንደ ሃይማኖቱ፣ ሙሐመድን መልእክተኛ አድርጎ ወዶ የተቀበለ በርግጥ የእምነትን ጣእም ቀምሷል)።
አዎን! አንድ ሰው በፈጣሪው እጅ ውስጥ መሆኑን ከተረዳ፣ እጅግ ያማሩ መልካም ስሞቹንና ምሉዕ የሆኑ ባህሪያቱ ካወቀ፣ ልክ እንደሚያየው አድርጎ ቢያመልከው፣ አምልኮውን በፍፁምነት ለአላህ ብቻ ካደረገ እና ከእርሱ ውጪ ያለን ሌላ አካል ካልፈለገ። በቅርቢቱ ዓለም መልካምና ደስተኛ ሕይወት በመጨረሻይቱም ዓለም መልካም ፍጻሜ ይኖረዋል።
በዚህ ዓለም ላይ በአማኝ ላይ የሚያጋጥሙትን መከራዎች እንኳን ሳይቀር ቃጠሏቸው በየቂን (በአላህ ላይ ባለን ሙሉ እምነት) ፣ የአላህን ውሳኔ ወዶ በመቀበል ይበርዳሉ፤ መልካምም ሆነ መጥፎ ስለ ቅድመ ውሳኔዎቹ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ወዶ በመቀበልና እርካታውን በመግለፅ ያመሰግናል።
አንድ ሙስሊም ደስታውና እርጋታው እንዲጨምረለትና እንዲጎለብትለት ሊያደርግ ከሚገባቸው ነገሮች መካከል አላህን ደጋግሞ በብዛት ማውሳት እና የተከበረውን ቁርኣን ማንበብ ይገኙበታል፤ ልክ አላህ እንዳለው፦﴿الَّذِينَ آمَنُوا وَتَطْمَئِنُّ قُلُوبُهُمْ بِذِكْرِ اللَّهِ أَلَا بِذِكْرِ اللَّهِ تَطْمَئِنُّ الْقُلُوبُ﴾ "(እነሱም) እነዚያ ያመኑ ልቦቻቸውም አላህን በማውሳት የሚረኩ ናቸው፡፡ ንቁ! አላህን በማውሳት ልቦች ይረካሉ፡፡"(አርረዕድ፡28)እናም አንድ ሙስሊም አላህን ማስታወስና ማውሳት እንዲሁም ቁርኣንን ማንበብ በጨመረ ቁጥር ከፍ ካለው አምላክ አላህ ጋ ያለው ቁርኝት እየጨመረ፣ ነፍሱ እየፀዳች እና እምነቱ ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል።እንደዚሁም አንድ ሙስሊሙ ኃያሉን አላህን በዕውቀትና በማስረጃ ላይ ሆኖ እንዲያመልክ ሃይማኖቱን ከትክክለኛ ምንጮች ለመማር ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ጥረት ሊኖረው ይገባል። ነብዩ አላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን እንዲህ ብለዋል፡-"ዕውቀትን መፈለግ በሁሉም ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው።"(የአንዳን ኢስላማዊ ድንጋጌዎችን) ጥበብ አወቀውም አላወቀም ለፈጠረው አምላክና ከፍ ላለው አላህ ትእዛዛት መገዛት እና ታዛዥ መሆን ይገባዋል።﴿وَمَا كَانَ لِمُؤْمِنٍ وَلَا مُؤْمِنَةٍ إِذَا قَضَى اللَّهُ وَرَسُولُهُ أَمْرًا أَنْ يَكُونَ لَهُمُ الْخِيَرَةُ مِنْ أَمْرِهِمْ وَمَنْ يَعْصِ اللَّهَ وَرَسُولَهُ فَقَدْ ضَلَّ ضَلَالًا مُبِينًا﴾ "አላህና መልክተኛውም ነገርን በፈረዱ ጊዜ ለምእምናንና ለምእምናት ከነገራቸው ለእነርሱ ምርጫ ሊኖራቸው አይገባም! የአላህንና የመልክተኛውንም ትእዛዝ የጣሰ ሰው ግልጽ የሆነን መሳሳት በእርግጥ ተሳሳተ።"(አል አሕዛብ፡36)
ምስጋና ለአላህ ይገባው, የዓለማት ጌታ ለሆነው, እና እዝነትና ሰላም በነቢያችን ሙሐመድ ላይ እና ቤተሰቡ እና በባልደረቦቹ ላይ ይውረድ
ተፈጸመ!
የርዕሶች ማውጫ
ቁጥር
ርዕስ
ገጽ
ወደ ሽፋን ለመመለስ
ወደ ርዕስ ማውጫው ይሂዱ
ከመጽሐፉ ጋ ያሎትን ተሞክሮዎ ያካፍሉን
እባክዎን ድህረገጹን ይጎብኙ
የሞባይል መስተጋብራዊ መጽሐፍ
ወደ ርዕሱ ለመሄድ ጠቅ ያድርጉ
ወደ ሽፋኑ ለመመለስ ምስሉን ጠቅ ያድርጉ
ባርኮዱን ይቃኙ
ትምህርታዊ አቀራረብ (ፓወርፖይንት)
የፕሮጀክት ምርቶች
የታተመ መጽሐፍ
የሞባይል መጽሐፍ
ድህረገጽ
የፓወርፖይንት አቀራረብ
የስማርትፎን ስሪት ብቻ