Description
አጭር ማጠቃለያ ስለእስልምናው መልእክተኛ ሙሐመድ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም
Ambeni abängbïngö nde 61
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ይህ መልዕክት ስለ እስልምናው ነብይ የአላህ መልዕክተኛ ሙሐመድየአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን፥ አጠር ባለ መልኩ የሚዳስስ ሲሆን ስማቸው፣ የዘር ሀረጋቸው፣ ሀገራቸው፣ የትዳር ሁኔታቸው፣ ተልዕኳቸው፣ የተጣሩበት ጉዳይ፣ የነብይነታቸው ተዓምራቶች፣ ይዘውት የመጡት መመሪያ እና ተቃዋሚዎቻቸውም ስለ እርሳቸው የነበራቸው አቋም ሁሉ ተዳሶበታል።
የእስልምናው ነብይ መልዕክተኛው ሙሐመድ ቢን ዐብዲላህ ቢን ዐብዱልሙጦሊብ ቢን ሃሺም የኢብራሂም ልጅ የሆኑት ኢስማዒል የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈን ዝርያ ናቸው።ይኸውም ነብዩላህ ኢብራሂም የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ልጃቸውን ኢስማዒልን እና ባለቤታቸው ሃጀርን ከታላቋ ሶሪያ ወስደው በአላህ ትእዛዝ መካ ላይ ያሰፈሯቸው በመሆናቸው ነው። ታዲያ እኚህ ታዳጊ ኢስማዒል አድገው ወጣት በሆኑ ጊዜ የአላህ ነብይ ኢብራሂም የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ወደ መካ መጡና ከልጃው ጋር ሆነው የተከበረውን የአላህ ቤት ካዕባን ገነቡ። ሰዎችም በዙሪያው መበራከት ጀመሩና መካ የዓለማቱ ጌታ አላህን የሚያመልኩ ሰዎች የሚያስቧት፤ ሐጅ ለማድረግም የተመረጠች ቦታ ሆነች። ሰዎችም ለዘመናት በኢብራሂም የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ጎዳና ላይ ሆነው አላህን በማምለክና እርሱንም በብቸኝነት በመገዛቱ ላይ ቀጠሉ።ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ከእስልምና ሃይማኖት ማፈንገጥ የተከሰተው። ማለትም ልክ በዙሪያዋ እንዳሉት የዓለም ክፍሎች የባዕድ አምልኮ፣ ሴት ህፃናትን መቅበር፣ ሴቶችንም መበደል፣ የቅጥፈት ቃል፣ አስካሪ መጠጥ መጠጣት፣ ብልግናን መፈፀም፣ የወላጅ የሞተባቸውን ህፃናትን ገንዘብና አራጣ መብላትና መሰል የባዕድ አምላኪዎች ስራ የተንሰራፋባቸው የሆኑት።የእስልምናው ነብይ ረሱል ሙሐመድ ቢን ዐብዲላህ የኢስማዒል ኢብኑ ኢብራሂም ዝሪያ የአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይህንን በሚመስል ማህበረሰብ ውስጥ ጊዜውም በ571 ዓ. ል ነበር የተወለዱት። አባታቸው ገና ሳይወለዱ የሞቱ ሲሆን እናታቸውም የስድስት ዓመት ህፃን እያሉ ነው የሞተችው። አጎታቸው አቡ ጧሊብ አሳደጋቸው፤ ላባቸውን ጠብ አድረገው በእጃቸው ሰርተው የሚበሉ የቲም፣ ሚስኪን ሆነው አደጉ።
እድሜያቸው ሃያ አምስት አመት ሲሞላ አላህ መልካም ስራዋን ይውደድላትና ከመካ ሴቶች መካከል ኸዲጃህ ቢንት ኹወይሊድ ከተባለች እመቤት (ልዕልት) ጋር ተጋቡ። ከእርሷም አላህ አራት ሴት ልጆችንና ሁለት ወንድ ልጆችን ለገሳቸው፤ ይሁን እንጂ ልጆቻቸው ገና በጨቅላነታቸው ነበር የሞቱት። ከባልተቤታቸውና ከቤተሰባቸው ጋር የነበራቸው አኗኗርም እጅግ በርህራሄና በፍቅር የተሞላ ነበር። ለዚህም ነበር ባለቤታቸው ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ እጅጉን ትወዳቸው የነበረው፤ እርሳቸውም ቢሆኑ ታዲያ ፍቅሯን በፍቅር ነበር የመለሱላት። ከሞተች ረጅም ዓመት አልፏት እንኳ አልረሷትም ነበር። ይልቁኑ ውዴታዋን ፀንቶ እንዲቆይ እና (ከሞተችም በኋላም) ለእርሷ በጎ ከመዋል አኳያ በግ ወይም ፍየል እያረዱ ስጋውን ለእርሷ ጓደኞች ያከፋፍሉ ነበር።
የአላህ መልዕክተኛው ሙሐመድ የአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ገና ከመፈጠራቸው ጀምሮ ባማረ ስነምግባር ላይ የታነፁ ነበሩ። ያደጉበት ማህበረሰብም "እውነተኛው ታማኙ" ብለው ይጠሯቸው ነበር። በታላላቅ ስራዎችም አብረዋቸው ይሳተፉ ነበር። እነርሱ ያሉበትን የባዕድ አምልኮ ስራ ግን አይሳቱፉበትም ነበር፤ ይጠሉባቸውም ነበር።
እድሜያቸው አርባ አመት በሞላ ጊዜ መልዕክተኛው እንዲሆኑ አላህ መረጣቸው። ከዚያም ጂብሪል የአላህ ሰላም በእርሱ ላይ ይስፈን መጀመሪያ የወረደውን የቁርኣን ሱራ (ምዕራፍ) ይዞላቸው መጣ። ይኸውም ተከታዩ የአላህ ቃል ነው፦(اقْرَأْ بِاسْمِ رَبِّكَ الَّذِي خَلَقَ (1) {አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም። (1)خَلَقَ الْإِنسَانَ مِنْ عَلَقٍ (2) ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)። (2)اقْرَأْ وَرَبُّكَ الْأَكْرَمُ (3) አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን፤ (3)الَّذِي عَلَّمَ بِالْقَلَمِ (4) ያ በብርዕ ያስተማረ። (4)عَلَّمَ الْإِنسَانَ مَا لَمْ يَعْلَمْ (5)) ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲሆን። (5)}[አል-ዓለቅ፥ 1-5]የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ልባቸው እየተርበተበተ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ቃል ይዘው ወደ ባለቤታቸው መጡ። ሁኔታውንም ተረኩላት፤ እርሷም አረጋጋቻቸውና ተውራትንና ኢንጂልን የሚያነብ ወደሆነው የአጎቷ ልጅ ወረቃህ ኢብን ነውፈል ይዛቸው ሄደች። "የአጎቴ ልጅ ሆይ! እስኪ ይህ የወንድምህን ልጅ የሚነግርህን ነገር ስማው።" አለች። ወረቃም ቀጠል አድርገው "የወንድሜ ልጅ ሆይ! እስኪ ንገረኝ" አሏቸው። የአላህ መልዕክተኛም የአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የሆነውን ሁሉ ተረኩላቸው። የዚህን ግዜ ወረቃህ እንዲህ አላቸው፦ይህማ በሙሳ ላይ የተወረደው ሚስጥረኛ እኮ ነው! ምነው አፍላ ወጣት ሆኜ በነበር! ምነው ህዝቦችህ ከሀገርህ ሲያስወጡህ ህያው ሆኜ በነበር!" ሲላቸው። የአሏህ መልዕክተኛም የአላህ ውዳሴ ና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን "ከሀገሬ ያስወጡኛልም እንዴ?!" አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ "አዎ! አንተ ይዘሀው የመጣሀውን ተልዕኮ ይዞ የመጣ ሁሉ ጠላት አጋጥሞታል። ያንን እለት አላህ ቢገጠመኝ የቁርጠኛን እርዳታ ነበር የምረዳህ።"
በመካ ሳሉም ቁርኣን ተከታትሎ ይወርድላቸው ነበር፤ ጂብሪልም ዓለይሂ ሰላም ከአላህ በሚመጣለት አኳኃን ተልዕኮውን ማድረሱን ቀጠለ።
እርሳቸውም ህዝባቸውን ወደ እስልምና መጣራታቸውን ቀጠሉ። ህዝባቸው ግን መቃወምና መከራከሩን ተያያዙት፤ ከዚያም አልፈው ገንዘብ፣ ንግስናን የመሳሰሉ ነገሮችን እንደመደለያ እያቀረቡ ተልዕኳቸውን እንዲተው ወተወቷቸው። ይሁን እንጅ የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይህንን ሁሉ አልቀበልም ብለው ተልዕኳቸውን ቀጠሉ። ህዝቦቻቸው በዚህ ሳይሳካላቸው ሲቀር ከዚያ በፊት የነበሩ መልዕክተኞች በህዛባቸው እንደተባሉት እርሳቸውም "ደጋሚ፣ ውሸታም፣ ቀጣፊ" ተባሉ ኖሯቸውንም ለማጨናነቅ (ለማመሰቃቀል) ጣሩ፤ የተከበረው አካላቸውም ላይ ድንበር አልፈው ጥቃት ሰነዘሩባቸው፤ ተከታዮቻቸውም አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ተደረጉ።ረሱል የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ግን ከዚህ ሁሉ መሰናክል ጋር በመካ ሆነው የሐጅ አጋጣሚዎችንና የዐረቦችን ወቅታዊ የግብይት ጊዜያቶችን እየተጠባበቁ ወደ አላህ ጥሪ (ዳዕዋ) የማድረግ ተልዕኳቸው ላይ ፀኑ። በዚያም ሰዎችንም እያገኙ እስልምናን ይጋብዟቸው በዱኒያዊ ጥቅማጥቅምም ይሁን በስልጣን ሳያስጎመጁ ‐ስልጣንም አልነበራቸውም ንጉስም አልነበሩም‐ በሰይፍም ሳያስፈራሩ ይልቁን እርሳቸው ይዘው የመጡት የተከበረውን ቁርኣን የመሰለ ነገር ይዞ መምጣት የሚችል ካለ እያሉ ውርርድ እያቀረቡ፤ ተቃዋሚዎቻቸውን እየተፎካከሩ ዳዕዋቸውን ቀጠሉ። በዚህም ከተከበሩት ሰሓቦች (ባረደቦቻቸው) መካከል አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ያመነው አመነላቸው።በመካ ቆይታቸውም ወቅት አላህ ወደ በይተል መቅዲስ (ኢስራእ) እና ወደ ሰማይ ጉዞ (ሚዕራጅ) በማስደረግ በታላቅ ተዓምር አከበራቸው። በክርስትናም በእስልምናም እንደሚታወቀው፥ አላህ ነብዩ ኢልያስንና መሲሑ ዒሳን የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጓቸዋል።ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የሰላትን መመሪያ የተቀበሉት ሰማይ ላይ በወጡበት ወቅት ነበር። ይህም ዛሬ ድረስ ሙስሊሞች ሁል ጊዜ በየቀኑ የሚሰግዱት የሆነው አምስቱ የሶላት ወቅት ነው። በተከበረችዋ መካ ቆይታቸው ሌላ ታላቅ ተዓምርን አስከስቶላቸዋልም። ይኸውም ሙሽሪኮቹም ጭምር በዐይናቸው ያዩት የሆነ የጨረቃ መሰንጠቅ ነው።
የመካ አጋሪዎችም (ሙሽሪኮችም) ሰዎችን ከእርሳቸው ለማሸሽና በክፉነታቸውም ለመፅናት እንዲያግዛቸው የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመዋል። እርሳቸውን በመከራከር እና ሰዎችንም ከእርሳቸው በመግታት ይረዳቸው ዘንድ በአይሁዶቹም ታግዘው የቁርኣንን አምሳያ ለማምጣት በከንቱ ልፋት ብዙ ተንገላቱ።
የመካ አጋሪዎችም (የሙሽሪኮች) ጭቆና በምእመናኑ ላይ በበረታ ጊዜ ነብዩም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ወደ ሓበሻ ምድር እንዲሰደዱ ለምእመናኑ ፍቃድ ሰጧቸው። ስለ ንጉሱም እንዲህ አሏቸው፦ "እርሱ ዘንድ ማንም የማይበደልበት ንጉስ አለና እርሱ ጋ ሂዱ።" ይህ ንጉስ በወቅቱ ክርስትያን ነበር። በዚህም ሁለት ቡድኖችም ወደ ሓበሻ ተሰደዱ። ታዲያ እነዚህ ሙሃጂሮች (ለሃይማኖታቸው የተሰደዱት) ወደ ሀበሻ እንደሄዱ ለዚህ ነጃሺይ የተባለው ንጉስ ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይዘውት የመጡትን ሃይማኖት አቀረቡለት። እርሱም እስልምናን ተቀበለ፤ እንዲህም አለ፦ "በአላህ ይሁንብኝ! ይህ እና ሙሳ ይዞት የመጣው ሃይማኖት ከአንድ ምንጭ የተቀዳው ነው ።" ህዝባቸውም በእርሳቸው እና በባልደረቦቻቸው ላይ መከራን አከታተሉባቸው።
የዛኔ በሚያደርጉት ወቅታዊ ዳዕዋዎች እስልምናን የተቀበሉ እርሳቸውንም እንደሚረዱ ቃል የተጋቡ ከመዲና የመጡ ሰዎች ነበሩ። በዚህም ወደ መዲና ሄዱ። በጊዜው "የሥሪብ" ተብላ ትጠራ ነበር። የተቀሩ መካ የሚገኙት ባልደረቦቻቸውንም ወደ ነብዩ መዲና እንዲሰደዱ ፈቃድ ሰጧቸው። እነርሱም ተሰደዱና እስልምናም በመዲና የእያንዳንዱን በር እስኪያንኳኳ ድረስ ይበልጥ ተስፋፋ።
ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን በመካ ዳዕዋ እያደረጉ ካሳለፉት የአስራ ሶስት አመት የዳዕዋ ቆይታ በኋላ ወደ መዲና ሂጅራ (ለእምነታቸው ነጻነት ሲባል ስደት እንዲወጡ) እንዲያደርጉ አላህ ለእርሳቸውም ፈቀደላቸው። እርሳቸውም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሂጅራ አድርገው ወደ አላህ የሚያደርጉትን ዳዕዋ ቀጠሉ። የእስልምና ሸሪዓም (ድንጋጌ እና መመሪያ) በተከታታይ ተራ በተራ መውረዱን ቀጠለ። እርሳቸውም የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ወደ ሀገር አስተዳዳሪዎችና ንጉሶች ዳዕዋውን የሚያስተጋቡ ወደ እስልምና ጥሪ የሚያደርጉ ልዑካንን መላክ ጀመሩ። ከላኩባቸው መካከልም፦ የሩም (የባይዛንታይኑ) ንጉስ፣ የፐርሽያው ንጉስ እና የግብፁ ንጉስ ይገኙበታል።
በመዲና እያሉም የፀሀይ ግርዶሽ ተከስቶ ሰዎች ተደናገጡ፤ የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ልጅ ኢብራሂም ከሞተበት ቀን ጋር ተገጣጠመ፤ የዚህ ጊዜ ታዲያ ሰዎች፦ "ፀሀይ የተጋረደችው እኮ ኢብራሂም በመሞቱ ነው" አሉ። ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ግን እንዲህ ነበር ያሏቸው፦"ፀሓይም ይሁን ጨረቃ ለማንም ሞትም ይሁን ውልደት አይጋረዱም፤ ይሁን እንጅ አላህ ባርያዎቹን የሚያስደነግጥባቸው (የሚያስፈራራበት) ተዓምራቶች ናቸው።"ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የውሸት ተጣሪ (ሰባኪ) ቢሆኑ ኖሮ፥ ይህንን አጋጣሚ በተጠቀሙበትና እንዲህም ባሉ ነበር፦ "ፀሀይዋ ልጄ በመሞቱ እየተጋረደች እኔን የሚያስተባብለኝ ሰው እንዴት ሊሆን ነው?!"
የአላህ መልዕክተኛ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ጌታችን አላህ ባማረ ስነምግባር አስውቧቸዋል፤ እንዲህ በማለትም ነው የገለፃቸው፦(وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ) {አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}[አልቀለም፡ 4]እንደ እውነተኝነት፣ ኢኽላስ (ከይዩልኝ ይስሙልኝ ሙሉ በሙሉ መራቅ)፣ ጀግንነት፣ ፍትሃነት፣ ከተቃዋሚዎቻቸውም ጋር ቢሆን ቃል አክባሪነት፣ ቸርነት፣ ለድሆችና ሚስኪኖች እንዲሁም ለችግረኞችና ባላቸው ለሞተባቸው ባለትዳሮች ምፅዋት መስጥት፣ ቀናውን ጎዳና እንዲይዙ መጓጓት፣ ለእነርሱ ማዘን እና መተናነስ በመሳሰሉ መልካም ስነምግባሮች ሁሉ የሚገለፁ ናቸው። እንግዳ የሆነ ሰው መጥቶ ከባልደረቦቻቸው መሀል ሆነው የሚለዩበት ነገር ባለመኖሩ "የትኛችሁ ነው ሙሐመድ?" ብሎ እስከመጠየቅ ይደርስ ነበር።
የህይወት ታሪካቸው፥ ከሁሉም ሰው ጋር ከወዳጅም ከጠላትም፣ ከቅርቡም ከሩቁም፣ ከትልቁም ከትንሹም፣ ከሴትም ከወንድም፣ ከእንስሳውም ከበራሪውም ጋር ሁሉ የነበራቸው ግንኙነት የምሉእነት እና የምጡቅ ስብእና ምልክት ነበር።
አላህ መልዕክቱን ባሟላላቸውና እርሳቸውም ተልዕኳቸውን በሚገባ ከተወጡ በኋላ እድሜያቸው ስልሳ ሶስት ሲሞላ ሕይወታቸው አለፈ። ከዚህ እድሜያቸው ዐርባው ነብይ ከመሆናቸው በፊት ሲሆን፥ ሃያ ሶስቱ ደግሞ ነብይም ረሱልም ሆነው ነው ያሳለፉት።በመዲና ተቀበሩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን። ሲሞቱ ሲጓጓዙባት ከነበረችው ነጭ በቅሏቸውና ለመንገደኛ ሰደቃ ምፅዋት አድርገው ከሰጡት መሬት ውጭ ለቤተሰቦቻቸው እንኳ ንብረትም ሆነ ውርስም አልተዉም ነበር።
በእርሳቸው አምነው እስልምናን የተቀበሉና የተከተሏቸውም ቁጥራቸው በርከት ብሎ ነበር። ከእስሳቸው ጋር አብረው የመሰናበቻ ሐጅ ያደረጉት እንኳ ከመቶ ሺህ በላይ ነበሩ። ይህም የሆነው ከሕልፈታቸው ሶስት ወር ቀደም ብሎ ነበር። በእስላማዊ እሴቶች እና መርሆዎች ላይ የኮተኮቷቸው (ያነጻቸው) ባልደረቦቻቸውም ከየትኛውም ባልደረባ ይበልጥ ፍትሀዊ፣ ዛሂድ፣ ቁጥብ፣ ቃላቸውን አክባሪ እና ለዚህ ሃይማኖትም ያላቸውን ይበልጥ የለገሱ ነበሩ። ምናልባትም ይህ የሃይማኖታቸው መጠበቅ እና መስፋፋት አንዱ ምስጢር ሳይሆን አይቀርም።
አላህ የሁሉንም መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና ከባልደረቦቻቸውም መካከል በእምነት፣ በእውቀት፣ በተግባር፣ በቅንነት፣ አምኖ በመቀበል፣ በጥረት፣ በጀግንነት እና በቸርነት እጅግ በላጮቹ፡- አቡበክር አስ-ሲዲቅ፣ ዑመር ቢን አል-ኸጣብ፣ ዑስማን ቢን ዐፋን እና ዐሊይ ቢን አቢጧሊብ ረዲየሏሁ ዓንሁም ናቸው። ገና ከጅምሩ በእርሳቸው ካመኑት እና እውነት ብለው ከተቀበሏቸው መካከልም ነበሩ። ከእርሳቸውም በኋላ የኢስላምን ባንዴራ የያዙትም ኸሊፋዎች እነዚሁ ናቸው። ይሁን እንጂ ለነብያት ብቻ ከተሰጡ መለያ ቅንጣትም አልነበራቸውም፤ ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ዘንድም ከተቀሩት ባልደረቦች እንረሱን ብቻ የለዩበት ነገር አልነበሩም።
አላህ፥ ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይዘውት የመጡትን ሱና፣ ታሪክ፣ ንግግርና ተግባር ልክ መጀመሪያውኑ ባስተማሩበት ቋንቋ ጠብቆላቸዋል። በታሪክ ማህደር የእርሳቸው ታሪክ እንደተጠበቀው የማንም ታሪክ አልተጠበቀለትም። እርሳቸው እኮ እንዴት እንደሚተኙ፣ እንዴት እንደሚበሉና እንዴት እንደሚጠጡና እንዴት እንደሚስቁ ጭምር ነው ታሪካቸው የተጠበቀው።ቤታቸው ውስጥ ከባለቤታቸው ጋር የነበራቸው መስተጋብር እንኳ እንዴት እንደነበር ተዘግቧል።የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሁኔታቸው ሁሉ በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል። እርሳቸው ሰው የሆኑ የአላህ መልእክተኛ ናቸው። ከአምላካዊ መገለጫም ቅንጣት እንኳ ድርሻ የላቸውም። ለራሳቸውም እንኳ ጥቅም የማምጣት እና ጉዳት የመከላከል ስልጣን የላቸውም።
አላህ ነብዩ ሙሐመድን የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የላካቸው ሺርክ፣ ክህደትና ድንቁርና በምድር ላይ ተንሰራፍቶና በምድር ላይም ከጥቂት የአህለል ኪታብ ቅሪቶች በቀር አላህን ምንም ሳያጋራ የሚያመልክ ማንም ባልነበረበት ወቅት ነው። አላህ በቅን መንገድና በእውነተኛ ሃይማኖት፥ በሃይማኖቶች ሁሉ ላይ የበላይ ሊያደርግበት ሰዎችንም ከጣዖት አምልኮ፣ ከክህደት እና ከድንቁርና ጨለማ ወደ ተውሒድ እና እምነት ብርሃን ሊያስወጣበት፤ የነብያቶችም የሩሱሎችም መደምደሚያ አድርጎ ወደ ዓለማት ሁሉ ላካቸው። መልዕክታቸው የቀደምት ነብያት ዓለይሂሙ ሰላቱ ወሰላም ተልዕኮ ማሟያ እንዲሆን ተደርገው ተላኩ።
ጥሪያቸውም ሁሉም ነብያትና መልእክተኞች ዐለይሂም ሰላም የተጣሩበት የሆነው ጥሪ ነበር። የኑሕ፣ የኢብራሂም፣ የሙሳ፣ የሱለይማን፣ የዳውድና የዒሳ ሁሉ ጥሪ - ብቸኛው አምላክ አላህ ፈጣሪ፣ ሲሳይ ለጋሽ፣ ህይወትን የሚሰጥና የሚነሳ፣ ንጉሠ_ነገሥት፣ ነገራቶችን ሁሉ የሚያስተናብረው እርሱ ነው ፣ እርሱ በጣም ርኅሩኅ አዛኝ ነው፣ በዓለማት ውስጥም የምናየውንና የማናየውን ነገር ሁሉ ፈጣሪው እርሱው መሆኑንና ከአላህ በስተቀር ያለው ሁሉ ከፍጥረታቱ መካከል የሆነ ፍጡሩ ብቻ ነው የሚል እምነት ነበር ጥሪያቸው።
አላህን በብቸኝነት ማምለክና ከእርሱ ውጪ ያሉትን ሁሉ ማምለክን መተው፣ አላህ አንድ መሆኑንና በተመላኪነቱም ይሁን በባለቤትነቱ፣ በፈጣሪነቱም ይሁን በአስተናባሪነቱ ምንም አጋር እንደሌለው እጅጉን ግልጽ በሆነ መልኩ ዳዕዋ አድርገዋል። የላቀው አላህ: ያልወለደም ያልተወለደም መሆኑን፤ የሚስተካከለው አቻም ይሁን አምሳያም የሌለው መሆኑን፤ በፍጡራኑ ምንም ነገር ውስጥ የማይሰርፅና የፈጠረውም ፍጡርን አካልም የማይላበስ መሆኑን ግልፅ አድርገዋል።
እንደ ኢብራሂምና ሙሳ ዓለይሂሙ ሰላም ሱሑፍ እንዲሁም ተውራት፣ ዘቡርና ኢንጅል በመሳሰሉ መለኮታዊ መጽሐፍት እንዲያምኑም ለሰው ልጆች ሁሉ ጥሪ አድርገዋል። እንዲሁም በመልክተኞችም ሁሉ ማመንና አንዱንም ነቢይ ያስተባበለም በነቢያት ሁሉ እንደካደ እጅጉን ግልፅ አድርገው ተጣርተዋል።
የሰው ልጆችን ሁሉ በአላህ እዝነት አብስረዋል፤ እንዲሁም ለመላው የዱኒያ ጣጣቸው ሁሉ አላህ እንደሚበቃቸው፣ አላህም አዛኝ ጌታ እንደሆነ፣ በእለተ ቂያማ ሁሉንም ከመቃብራቸው ቀስቅሶ ፍጡራንን የሚተሳሰባቸው እንደሆነ፣ ምእመናንንም በመልካም ስራዎቻቸው አስር እጥፍ አድርጎ እንደሚመነዳቸው፣ ለሰሩት ክፋት ግን በስራቸው ልክ ብቻ እንደሚተሳሰብና በአኺራ ህይወታቸውም ዘልዓለማዊ ፀጋ እንደሚያጣቅማቸው አብስረዋል። ከከሀዲያን ሆኖ ክፋትንም ለሚሰራ ደግሞ በዱኒያም በአኺራም የስራውን ቅጣት እንደሚያገኝ ሁሉ አስተምረዋል።
እንዲሁም መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - በተሰጣቸው ተልዕኮ ጎሣቸውን፣ አገራቸውን፣ ክቡር ነፍሳቸውን እንኳ ለማላቅ አልተጠቀሙበትም። ይልቁንም በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ የነቢዩላህ ኑሕ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ እና ዒሳ ዐለይሂ-ሰላም ስም የእርሳቸው ስም ከተጠቀሰው በላይ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። የእናታቸውም ሆነ የሚስቶቻቸው ስም በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ አልተጥቀሰም የሙሳ እናት ስም ግን በቁርኣን ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፤ የመርየም የአላህ ሰላም በእርሷ ላይ ይስፈን ስም ደግሞ ሰላሳ አምስት ጊዜ ተወስቷል።
እንዲሁም መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - የአላህን መመርያ፣ ምክንያታዊነትን እና ተፈጥሮን ወይም መልካም ስብእናን ከሚቃረኑ ነገሮች ሁሉ የተጠበቁ ናቸው። ምክንያቱም ነብያት ተልዕኳቸውን የማድረስ ኃላፊነት አላህ የሰጣቸው በመሆናቸውና በሚያደርሱትም ነገር ከአላህ ጥበቃ የሚደረግላቸው በመሆናቸው ነው። ነቢያቶች የጌትነት ወይም የመለኮትነት ባህሪያት የላቸውም። ይልቁንም እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ እነርሱም ሰዎች ሆነው ነገር ግን የላቀው አላህ የመልእክቱን ወሕይ (መለኮታዊ ራዕይ) የሚያወርድላቸው ናቸው።
የመልእክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን መልእክት በትክክል ከአላህ የሆነ ወሕይ ለመሆኑ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ታላላቅ ማስረጃዎች መካከል አስተምህሮታቸው ዛሬም ድረስ እርሳቸው በሕይወት እያሉ ይተገበር በነበረው ሁኔታ የዘለቀ መሆኑ ነው። ይሀው ይዘውት የመጡት አስተምህሮ ከቢሊዮን በላይ ሙስሊሞች እየተከተሉት፤ እንደ ሰላት፣ ዘካ፣ ጾም፣ ሐጅ እና ሌሎችንም ሳይቀይሩና ሳያዛቡ ሃይማኖታዊ ግዴታዎች ዛሬም ድረስ እየተተገበሩ ይገኛሉ።
አላህ ነብያትን ነብይነታቸውን በሚያመላክቱ ማስረጃዎች ደግፏቸዋል። መልእክታቸውንም በማስረጃዎች እና በመረጃዎች ያጠናክራል። እያንዳንዱ ነብይም የሰው ልጅ ሊያምንበት የሚችልን ተአምር ተሰጥቶታል። ነብያት ከተሰጧቸው ታላላቅ ተዓምሮችም እጅግ ታላቁ ተዓምር ነብያችን ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የተሰጡት ተዓምር ነው። አላህ እንደ ተአምር የሰጣቸው ቁርኣንን ነውና። ይህም ከነብያት ተዓምር እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ የሚዘልቅ ብቸኛው ተዓምር ነው። በእርግጥ ነብያችን ሙሐመድን የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ከዚህ ውጪ በሆኑ ታላላቅ ተዓምራትም አግዟቸዋል። የአሏህ መልእክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የተሰጧቸው ተዓምሮች እጅግ በርካታ ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል፡-
የሌሊት ጉዞ እና ማረግ (ኢስራእና ሚዕራጅ)፣ የጨረቃ መሰንጠቅ እና ህዝቡ ድርቅ እየገጠማቸው በነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ዱዓእ ለበርካታ ጊዜ አሏህ ዝናብ ማውረዱ።
ጥቂት የነበረውን የሚበላ ወይም የሚጠጣም ነገር ለብዙ ሰዎች እንዲበሉና እንዲጠጡ በሚችሉበት ብዛት ማበራከታቸው።
ማንኛውም ሰው ዝርዝር ሁኔታቸውን የማያውቃቸውን ከዚህ በፊት ያለፉ ጉዳዮች፣ ቀደምት ነብያት የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈን ከህዝቦቻቸው ጋር ያሳለፉት ታሪክ እና መሰል ጉዳዮችን አሏህ አሳውቋቸው መናገራቸው።
ጥራት ይገባውና የላቀው አሏህ አሳውቋቸው ልክ በሒጃዝ ምድር ተከስቶ በሻም ያሉ ሰዎችም ጭምር የተመለከቱት ከባድ የእሳት ቃጠሎ እና የሰዎችም በፎቅ መፎካከር መሰል ለወደፊቱ ይከሰታሉ ብለው ተንብየው የተከሰቱ እውነታዎች።
ከአላህ የተደረገላቸው ጥበቃና ከሰዎችም ያደረገላቸው ከለላ።
የሚከተሉትን የመሰሉ ለባልደረቦቻቸው የገቧቸው ቃላት እውን መሆን፦(ፐርሽያዎችንና ባይዛንታይኖችን ድል ታደርጋላችሁ፤ ድልባቸውም ለአላህ መንገድ ይውላል።)
የላቀው አላህ በመላእክቶች እገዛ ያደረገላቸው መሆኑ።
ነብያቶች የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይስፈን ስለ መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - አስቀድመው የምስራች መናገራቸው፦ ከእነዚህም ነብያት መካከል ሙሳ፣ ዳውድ፣ ሱለይማን፣ ዒሳ የአላህ ሰላም በሁሉም ላይ ይስፈን እና ሌሎችም የበኒ ኢስራኢል ነብያትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
ሰላማዊ አእምሮዎች በሚስማሙበት አሳማኝ ምክንያታዊ ማስረጃዎችም እገዛ ተደርጎላቸዋል።
ይህን መሰል አንቀጾች፣ ማስረጃዎች እና አመክንዮአዊ ምሳሌዎች በተከበረው ቁርኣንና በነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሱና ውስጥ ተገልፀው ይገኛሉ። ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የሰሯቸው ተአምራቶች ከገደብ በላይ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ሰፋ አድርጎ ለማወቅ የሚፈልግ እጅግ የተጣራ እርግጠኛ የሆነ እውነታውን ሊያገኝበት ዘንድ የተከበረው ቁርኣንን፣ የሱና ኪታቦችንና የነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን የታሪክ መጽሐፎችን ይመልከት።
እነዚህ ታላላቅ አንቀጾች እውን ባይሆኑ ኖሮ በአረብያ ባህረ ገብ የነበሩ ተቀዋሚ ከሀዲያን ቁረይሾች፣ አይሁዶችና ክርስትያኖች ነብዩ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ለማስተባበል አጋጣሚውን ይጠቀሙበት ነበር።
የተከበረው ቁርኣንም አላህ ለመልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ያወረደው መጽሐፍ፤ የዓለማቱ ጌታ ቃል ነው። አሏህም በቁርአኑ የሰው ልጆችንም ጂኒዎችንም አምሳያውን ወይንም ቢያንስ ከአምሳያው ሊመስል የምትችል አንዲት ሱራን እንኳ ማምጣት ይችሉ እንደሁ ለውርርድ ጋብዟቸዋል። ውርርዱ ዛሬም ቢሆን እንደቀጠለ ነው። የተከበረው ቁርአን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ግራ ለተጋቡባቸው በርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ይዟል። ታላቁ ቁርኣን በወረደበት ዐረብኛ ቋንቋ እስከ ዛሬም ድረስ ልክ በወረደበት ጊዜ እንደነበረው አንዲት ሆሄ እንኳ ሳይጨመር ሳይቀነስበት ተጠብቆ ይገኛል። ታትሞም የተሰራጨ ከሰው ልጆች አቅም በላይ የሆነ ታላቅ መጽሐፍ ነው። ለሰው ልጆች ከመጡላቸው መጽሐፎች መካከል ታላቁ ኪታብም ነው። በመሆኑም ሊነበብ ወይም መልዕክተ ትርጉሙ ሊነበብ የሚገባ መጽሐፍ ነው። ቁርአንን ማንበብ የቀረበት ሰው እንዳለ መልካም የሚባል ነገር ሁሉ ነው የቀረበት።ልክ የመልእክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን "ሱና" (ፈለግ)፣ መመሪያቸው፣ ታሪካቸው ሁሉ በታማኝ የዘጋቢዎች ሰንሰለት መሰረት ተጠብቆ የሚገኝ እንደሆነው ሁሉ ማለት ነው። መልዕክተኛው ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን በተናገሩበት ቋንቋ ዐረብኛ በመካከላችን እንዳሉ ሆኖ በህትመት ደረጃም የተሰራጨ ነው። ወደ በርካታ ቋንቋዎችም ተተርጉሟል። የተከበረው ቁርአንና የረሱል የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ሱና ለእስልምና እና ለመመርያው ብቸኛ ምንጮቹ ናቸው።
መልእክተኛው ሙሓመድ ‐ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ‐ ይዘውት የመጡት ሸሪዓ የእስልምና መመርያ ሲሆን የመለኮታዊ ህግጋቶች እና መለኮታዊ ተልዕኮዎ መደምደሚያ ነው። አመጣጡም ምንም እንኳ በዝርዝር አኳኃናቸው ቢለያዩም በመሰረቱ ከቀደምት ነብያት ህግጋቶች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነው።
ለሁሉም ጊዜና ቦታ የሚመጥን (የሚስማማ)፤ ለሰው ልጆች የዱኒያዊም የአኺራዊም ህይወታቸው ማስተካከያ ሙሉ መመርያ ነው። የዓለማት ጌታ የሚመለክባቸውን እንደ ሶላት፣ ዘካና መሰል በሰው ልጆች ላይ ግዴታ የሆኑ አምልኮዎችንም ሁሉ ያጠቃልላል። ለሰው ልጆች አስፈላጊ የሆኑ የተፈቀዱና የተከለከሉትን የገንዘብ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ፣ የወታደራዊ እና የአካባቢ ግብይቶች አበጥሮ ያብራራላቸዋል።
ይህ ሸሪዓ የሰዎችን ሃይማኖት፣ ደም፣ ክብር፣ ገንዘብ፣ አእምሮ እና ዘራቸውንም ይጠብቅላቸዋል። ሁሉንም መልካም ምግባራት እና ፅድቅን ያጠቃለለ ሲሆን ከማንኛውም ወራዳነት እና ክፋትም የሚያስጠነቅቅ ነው። የሰው ልጅንም ወደ ክብር፣ ሚዛናዊነት፣ ፍትሃዊነት፣ ከይዩልኝና ይስሙልኝ ርቆ ለአሏህ ብሎ መስራት፣ ንፅህና፣ ብልሀት፣ መዋደድ፣ ለሰዎችም መልካሙን መውደድ፣ ደም መፋሰስንም እንዲያስቀሩ፣ የሀገራቸውንም ሰላም እንዲያስጠብቁ ጥሪ የሚያደርግ ሲሆን ሰዎችን አላግባብ ከማስደንገጥና እንዲሰጉ ከማድረግም ያስጠነቅቃል። መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ለሁሉም ድንበር ማለፍን እና ብክለት (ብልሹነት) በአይነትና ቅርፁ ተፋላሚው ነበሩ። የእንቶ ፈንቶ እምነት፣ ከማህበረሰቡ ራስን ማግለልንና መምንኩስናን ይቃወሙ ነበር።
እንዲሁም መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - አላህ የሰው ልጅን - ወንድንም ይሁን ሴትን - እንዳከበረ እና መብታቸውንም ሁሉ እንዳረጋገጠላቸው፤ በምርጫቸው ፈልገው ለሚያደርጉት ድርጊትም እንቅስቃሴም ኃላፊነቱ እንዳለባቸው፤ ራስንም ይሁን ሌላን በሚጎዳ ድርጊትም ተጠያቂነት እንዳለባቸው ግልፅ አድርገዋል። በሃይማኖቱ ወንድም ይሁን ሴት ከእምነት፣ ከኃላፊነት፣ ከሽልማትና ምንዳ አኳያ እኩል ናቸው። በዚህ ሸሪዓ ውስጥ ሴት እንደ እናትም፣ እንደ ሚስትም፣ እንደ ሴት ልጅም እንደ እህትም ስትሆን የሚገባትን ልዩ ትኩረት ተችራለች።
እንዲሁም መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ይዘውት የመጡት ሸሪዓ አእምሮን ከመጠበቅ አኳያ እንደ አስካሪ መጠጥ አይነት የሚያበላሹትን ነገሮች ሁሉ ሐራም (እርም) አድርጓል። እስልምና ሃይማኖትን ለአእምሮ ብሩህነት አስፈላጊ የሆን ብርሃን አድርጎ ይቆጥረዋል። በዚህም ማንኛውም ሰው ጌታውን በአስተዋይነት እና በእውቀት ሆኖ ያመልከዋል። በእስልምና መመርያ የአዕምሮ ደረጃ ከፍ ያለና የኃላፊነትም ወሳኙ ማዕከል ነው። ከአጉል እምነት እና ጣኦታዊነት እስራትም ነፃ አውጥቶታል።
የእስልምና መመርያ ትክክለኛ ሳይንስን ይቀበላል፣ ከስሜታዊነት የጠራ ሳይንሳዊ ምርምርን እንዲካሄድም ያበረታታል፣ ስለ ራስም ስለ ፍጥረተ ዓለምም ወደ ማሰላሰል ጥሪ ያደርጋል። ትክክለኛ ሳይንሳዊ ውጤቶችም መልእክተኛው የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይዘውት ከመጡት ጋር የሚጣረስ አይደለም።
በእስልምና መመርያ (ሸሪዓ) ውስጥ አንዱ ጎሳ ከሌላኛው ጎሳ፣ አንዱ ህዝብም ከሌላኛው ህዝብ የሚበላለጥበት አንዳች ልዩነት የለም። ይልቁንም ሁሉም በኢስላማዊ ሸሪዓ ፊት እኩል ናቸው። ምክንያቱም ሁሉም ሰዎች በአፈጣጠራቸው እኩል ናቸውና። አንዱ ዘር ከሌላኛው ዘር ህዝብም ከህዝብ የሚበላለጥበት ሚዛን ቢኖር አሏህን በመፍራት ብቻ ነው። መልእክተኛው ሙሀመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ሁሉም ልጅ በተፈጥሮው በእስልምና ላይ ሆኖ እንደሚወለድም ተናግረዋል። በመሆኑም ማንም ቢሆን በስህተት ላይ ሆኖ አልያም ኃጢአትን ወርሶ የሚወለድ የለም።
በእስልምና መመርያ አሏህ "ተውባ" (ንስሀን) ደንግጓል፤ ይሀውም፡- የሰው ልጅ ኃጢአቱን ትቶ ወደ ጌታው በመመለስ፤ እስልምናን ከመቀበሉ በፊት የነበሩትን ወንጀሎች ደግሞ እስልምና በተቀበለበት ጊዜ ይሰረዝለታል። ለዚህም በሰው ልጅ ፊት የሰውን ሀጢያት መናዘዙ አስፈላጊ ባለመሆኑ እስልምና ከልክሎናል። በእስልምና የሰው ልጅ ቁርኝቱ ቀጥታ ከአምላኩ ጋር ነው። በአንተ እና በአሏህ መካከል አማላጅ አያስፈልግህም። እስልምና የሰው ልጅን አምላክ ወይም ከአሏህ ጌትነት አልያም መለኮታዊነት ድርሻ ከማድረግም ሐራም አድርጓል።
እንዲሁም መልእክተኛው ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ይዘውት የመጡት ሸሪዓ ከእርሳቸው በፊት ያለፉትን ሸሪዓዎች በሙሉ የሚሽር ነው። ምክንያቱም መሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ከአላህ ዘንድ ይዘውት የመጡት የእስልምና ሸሪዓ እስከ እለተ ፍፃሜ ድረስ ለዓለማቱ ሁሉ የመጨረሻው ሸሪዓ ነውና። ስለዚህም ከእርሱ በፊት የነበሩ ሸሪዓዎችን በሙሉ የሚሽር ሆነ። በዚህም መሰረት ኃያሉ አላህ የአሏህ መልዕክተኛ ሙሐመድ የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን ይዘውት ከመጡት የእስልምና ሸሪዓ ውጪ ሌላ ሃይማኖትን አይቀበልም፤ ስለዚህም ከእስልምና ሌላ ሃይማኖት የተከተለ ሃይማኖቱ ተቀባይነት የለውም። በዚህ ረገድ ሰፋ ያለ ዝርዝር ማብራርያ የፈለገም የዚህን ሸሪዓ ድንጋጌዎች ዝርዝር በተመለከተ እስልምናን በሚገልጹ ታማኝ መጽሐፍትን ይመልከት።
የእስልምና ሸሪዓ ግብ - ልክ እንደ ሁሉም መለኮታዊ ተልዕኮዎች ግብ ሁሉ፡- የሰው ልጅ እውነተኛው ሃይማኖት ተቀብሎ የአለማቱ ጌታ የአላህ ንፁህ ባሪያ እንዲሆን እና ለሰው፣ ለቁስ ወይም ለአጉል እምነት ባርያ ከመሆን መታደግ ነው።
የእስልምና ሸሪዓ ለማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚመጥን (የሚስማማ) ነው። በመሆኑም የሰውን ትክክለኛ ጥቅም የሚጻረር አንዳችም ነገር የለውም። ምክንያቱም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ከሚያውቅ ከአላህ ዘንድ የተወረደ ነውና። ሰዎች ትክክለኛ መመርያ ያለው ሃይማኖቱ ይፈልጋሉ። እስልምና ደግሞ እርስ በራሱ የማይጣረስ፣ የሰው ልጆችን የሚያስተካክል፣ ማንኛውም የሰው ልጅ ሊደነግገው የማይቻለውና ይልቁንም ከአሏህ ዘንድ የመጣ፣ ሰዎችንም ወደ መልካምነትና ወደ ቀናነት የሚመራ፣ ወደ እርሱም የተመሩ እንደሆነ ጉዳያቸውን አስተካክሎ አንዱ ሌላኛውን ከመበደል የሚታደጉበት ሃይማኖት ነው።
ሁሉም ነብያት የሚቃወማቸውና በጥሪያቸው መንገድ ላይ (ተደንቅሮ) የሚደቀንባቸው፣ ወደ ጥሪያቸውም ከመሄድ ሰዎችን የሚገታ ጋሬጣ እንዳጋጠማቸው የማያወላዳ እውነታ ነው። የአላህ መልእክተኛም ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - በህይወት ዘመናቸውም ይሁን ከህልፈታቸውም በኃላ ብዙ ተቃዋሚዎች ነበሯቸው። ይሁን እንጂ አላህም በሁሉም ላይ ረድቷቸዋል። የብዙዎቹ ምስክርነት - የጥንቶቹም ይሁን የአሁኖቹ - ነቢይ መሆናቸውን፤ ይዘውት የመጡትም መመርያ ቀደምት ነብያት የአላህ ሰላም በሁሉም ላይ ይስፈን ይዘውት እንደመጡት አይነት መለኮታዊ መመርያ መሆኑን ነው። እርሳቸው ትክክል እንደሆኑ ያውቃሉ ነገር ግን አብዛኛዎቹ በእርሳቸው እንዳያምኑ በብዙ መሰናክሎች ተከበዋል፤ ለምሳሌ የስልጣን ፍቅር ወይም ማህበረሰባቸውን መፍራት ወይም በዝና ያገኙትን ንብረት እንዳያጡ መስጋት ይገኙበታል።
ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን።
ጸሐፊ መምህር ዶክተር ሙሐመድ ቢን ዓብደሏህ ሱሐይም
በኢስላማዊ አስተምህሮ ክፍል የቀድሞ የዓቂዳ አስተማሪ
መሊክ ሰዑድ ዩኒቨርሲቲ ተርቢያ የትምህርት ክፍል
ሪያድ ከተማ ሳዑዲ ዓረቢያ
የኢስላም መልዕክተኛ ሙሐመድ የአላህ ውዳሴ እና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን
1‐ ስማቸው፣ የዘር ሀረጋቸው እና ተወልደው ያደጉበት ሀገር
2‐ የተባረከ ጋብቻ ከተባረከችዋ እመቤት (ልዕልት) ጋር
5- የነቢይነታቸው ተዓምራቶች፣ ምልክቶች እና ማስረጃዎቻቸው
6- ነቢዩ ሙሐመድ - የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን - ይዘውት የመጡት ሸሪዓ (መመርያ):-